FB_IMG_1665320609724

መንግሥት የተወሰኑ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ ክልከላ ሊጥል መሆኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ናቸው፡፡

ገዥው ይህን የተናገሩት መንግሥት የዋጋ ንረቱንና ሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ዝውውርን ለመከላከል፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን በአግባቡ ለመጠቀም ሲባል ብሔራዊ ባንክ የሚስዳቸውን የተለያዩ ርምጃዎችን በዘረዘሩበት ወቅት ነው፡፡

ዶክተር ይናገር በተለይ ከውጭ ወደ አገር የሚገቡ አንዳንድ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የሚወስን መመርያ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው በርካታ ምርቶች ከውጭ የምታስገባ መሆኑን ያስታወሱት ገዥው፣ እነዚህ ምርቶች መግባታቸው ጥሩ ቢሆንም አሁን ካለው የውጭ ምንዛሬ እጥረትና ከአስፈላጊነታቸው አንፃር ታይቶ፣ አንዳንድ ምርቶችን ከውጭ እንዳይገቡ ክልከላ ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡ ምርቶቹም በቅርቡ በሚወጣ መመርያ በዝርዝር የሚቀርቡ መሆናቸውን የገለጹት ገዥው፤ በዚህ መሠረት አንዳንድ ምርቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይገቡ ክልከላ እንደሚጣልባቸው አስረድተዋል፡፡

ከአስፈላጊነታቸው አንፃር ተመዝነው ክልከላ ይደረግባቸዋል የተባሉ ምርቶች ባይገለጹም፣ የትኞቹ ምርቶች በዚህ መመርያ ውስጥ እንደሚካተቱ በቅርቡ ይታወቃል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ብሔራዊ በፍራንኮ ቫሉታ አማካይነት ዕቃዎችን ወደ አገር የሚያስገቡ ግለሰቦች፣ የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሪ የራሳቸው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ የባንክ ስቴትመንት እንዲያቀርቡ የሚያስገድደውን አሠራር እንደገና መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ይህን ርምጃ የወሰደው በፍራንኮ ቫሉታ ዕቃ እናስመጣለን በማለት ከጥቁር ገበያ ዶላር እየገዙ መልሰው በማስወጣት እየሠሩ ያሉ መኖራቸውን ማረጋገጥ በመቻሉ እንደሆነ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ዕቃ የሚያስመጡበት ዶላር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የጥቁር ገበያ ጋር የተያያዘ አለመሆኑም ይጣራል ተብሏል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ብሔራዊ ባንክ በፍራንኮ ቫሉታ ለሚገቡ ዕቃዎች የሚውለው የውጭ ምንዛሪ፣ በትክክል ዕቃዎቹን ያስመጡ ግለሰቦች በውጭ ባንክ አካውንታቸው ውስጥ መኖር አለመኖሩን ያረጋግጥ ነበር፡፡ ገንዘቡ ከጥቁር ገበያው ጋር የተያያዘ አለመሆኑን በማረጋገጥ ዕቃውን ማስገባት እንደሚችሉ፣ ብሔራዊ ባንክ ለጉምሩክ ኮሚሽን በመጻፍ ይከናወን እንደነበርም ይናገር (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ይህ አሠራር ተመልሶ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን አስታውቀዋል ስል ሪፓርተር ዘግቧል ።