አፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ጥረት ከምንጊዜውም በላይ ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልጋት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለፁ።

የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቷ አንገብጋቢ የሆነውን የምግብ ዋስትናን እና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን በተመለከተ ዛሬ ጉባኤ አካሂዷል።

በጉባኤው የአፍሪካ አገራት ተወካዮች፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ፌዴሬሽንና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትና ችግር እየተባባሰ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ችግሩ በአፍሪካ ጎልቶ እንደሚታይ ተመላክቷል።

ለዚህም ዋነኛ መንስኤ ተብለው የተቀመጡት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት፣ በአህጉሪቷ በየቦታው እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ናቸው።

በዚህም እ.አ.አ በ2021 መረጃ መሰረት በአፍሪካ 278 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለረሃብ የተጋለጠ መሆኑ ተገልጿል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ጥምረት (አግራ) የቦርድ ሊቀመንበር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት አፍሪካ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል።

‘የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት የአፍሪካን ግብርና ክፉኛ እየተፈታተነው መሆኑን በማንሳት ይህን ተከትሎ የበርካታ አፍሪካ አገራት ዜጎች በቀን አንድ ጊዜ ምግባቸውን መሸፈን እንዳቃታቸው አመላክተዋል ።

ከአየር ንብረት ለውጥ በተጨማሪ በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች፣ የማዳበሪያ ፣ የምግብና የነዳጅ ዋጋ መጨመር በአህጉሪቱ  ምርትና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉን አንስተዋል።

በአፍሪካ የሚስተዋሉት የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረትና ሌሎች ተጨማሪ ችግሮች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ስርዓተ ምግብን ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት እንዳስተጓጎሉት ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጋራ በመሰባሰብና ወጥ የሆነ የአሰራር መንገድ በመከተል ድጋፋቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና በስንዴ ምርት ለአፍሪካ ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን በማንሳት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ይህን ተሞክሮ ማስቀጠል አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት የግብርናና ገጠር ልማት፣ የሰማያዊ ኢኮኖሚና ቀጣይነት ያለው ከባቢ ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ በበኩላቸው፣ በአፍሪካ የሚታየውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት በአንድነት የምንነሳበት አስገዳጅ ወቅት ላይ ነን ብለዋል።

አሁን ላይ በሩሲያና በዩክሬን መካከል የተከፈተው ውጊያ የምግብ ዋስትና ላይ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ችግር መፍጠሩን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተቋማት ለአህጉሪቷ የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲጨምሩና የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

የኖርዌይ የዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር አኒ ቤይዚ ቲቪነሪም፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ የአፍሪካ አገራት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ ፈተና እንደሆነባቸው አንስተዋል።

የአፍሪካ ህብረት የአህጉሪቱን ህዝብ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥና ስርዓተ ምግብን እውን የማድረግ ጉዳይ የዓለም ቀዳሚ አጀንዳ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ነው የተናገሩት ስል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: