በዎላይታ፣ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ ካሉት ስድስት ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች በምርጫ ቦርድ ልካሄድ በታሰበው ህዝበ ውሳኔ ላይ ዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ዎሕዴግ መግለጫ አውጥቷል። ግንባሩ ያወጣውን ሙሉ መግለጫ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደሚከተለው ልኳል።

በዚህ ሳምንት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አዲሱ ክልል በተባለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚካተቱ ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ገድኦ፣ ኮንሶ ዞኖችንና አሌ፣ ቡርጂ፣ አማሮ ኬሌ፣ ባስኬቶ፣ ልዩ ወረዳዎችን አንድ ላይ ጨፍልቆ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል ክልል ውስጥ ለማደራጀት በብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ መሠረት ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ህዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም ጥር 29/2015 ዓ.ም ቀን ቆርጫለሁ ሲል ማስታወቁን ሲንሰማ እጅግ አዝነናል ተገርመናል፡፡

የዎላይታ ህዝብ ከሶስት አመት በፊት ከቀበሌ ድረስ በወረደ አካታች የህዝብ ውይይት በተወሰነ ውሳኔ በምክር ቤት ተወካዮቹ አማካኝነት የክልል እንሁን ጥያቄውን እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ መላኩ ይታወሳል። ዎላይታ ዞን ምክር ቤት ህገ መንግስት በሚፈቅደው አካሄድ በ2012 ዓ.ም ይግባኝ የጠየቀውን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ያለ ህዝብ ፍላጎት የሻረው ምክር ቤት የስልጣን ጊዜ የጨረሱ መሆናቸውንና ዎላይታ ሕዝብን መወከል የማይችሉ መሆናቸውንና በነዚህ ሰዎች የተወሰነ ውሳኔ ህዝብን እንደማይወክል ልብ ማለት ይገባል። የክልል አደረጃጀት ህዝበ ውሳኔ ይደረግ ተብሎ ለምርጫ ቦርድ ስተላልፍ ህዝብን ጥያቄ ታሳቢ ያደረገና ህዝብን የሚያከብር ብሆን በምርጫ ውስጥ ከዚህ ቀደም ራሳቸውን በክልል ለማደራጀት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡ ሁሉም ዞኖች የዎላይታን ጨምሮ የህዝቤ ውሳኔ ምርጫ ፍላጎት ያካተተና ህዝበ ውሳኔው መራጭ ሕዝብ አሳታፊና አካታች መሆን ይገባል።

ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ምንድን ነው?

ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ማለት የመራጮች ሀሳብና ተጨማሪ አከራካሪ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ህዝብ በቀጥታ ድምጽ የሚሰጥበት ሥርአት ነው። ህዝበ ውሳኔ ማለት የፖለቲካ ጥያቄውን ሁሉም አማራጮች ተቀምጦበት ህዝቡ በድምፅ የሚያፀድቅበት ወይም የሚያፈርስበት የተለየ ህጋዊ መንገድ ሆኖ በተወካዩ ድምጽ ከሚወሰንበት ጉዳይ ጋር ተቃራኒ ነው። ስለዚህ ሕዝበ ውሳኔ ማለት አንድ የተለየ አከራካሪ ለሆነው ዓላማ ላይ ህዝቡ በአብላጫ ድምፅ የማጽደቅ ወይም ውድቅ ለማድረግ የመራጮች ሥልጣን ነው። መራጩ ሕዝብ ሊመርጥ ያሰበው ሁለትና ከዛ በላይ አከራካሪ ጉዳይ አማራጭ ሆኖ በግልጽ አስካልተቀመጠ ድረስ ህዝበ ውሳኔ ትርጉም የለውም፡፡ እንደዎላይታ ህዝብ ጥያቄ ሀ/ዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መሆን ለ/በክላስተር መደራጀት ሐ/ በደ/ብ/ብ/ሕ/ክልል መቀጠል የሚል የያዘ አማራጭ እስካልተያዘ ድረስ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው እንጂ ህዝበ ውሳኔ ልባል አይችልም፡፡ በእንደዚህ መልክ የቀረበ እንደሆነና ህዝበ ውሳኔ የሚተላለፈው አብዛኛዎቹ መራጮች በነቅስ ስሳተፉ በአብላጫ ድምጽ ከፀደቀ ብቻ ነው ህጋዊነትና ተቀባይነት የሚኖረው ፡፡ ነገር ግን በፌዴሬሽን ም/ቤት በኩል ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም እንዲከናወን ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ሁለት አማራጭ በፍጹም የሕዝብ ጥያቄ አማራጭ ሆኖ ካልቀረበ በስተቀር የህዝብ ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ማስመሰል ፖለቲካዊ አካሄድ ትውልድን የፖለቲካ ጥያቄ ወደ ቀጣይ ትውልድ ያሸጋገረ የህዝብ ጥያቄ የማይመልስ ቸልተኝነት የተካለበት የህዝብን የማስታወስ አቅም መናቅ፣ አለአግባብ የመንግስትን ሃብት ማባከን እና የተከፈለውን የትግሉ ሰማዕታት ነፍስ ላይ መቀለድ ነው።
የሀገርቱ ህዝብ መብት ለማስፈጸም በህገ መንግስት መርሆችን ተከትሎ እንዲያሰፈጽም የተቋቋመው ፌዴረሽን ምክር ቤት እና በህግና በህዝብ ፍላጎት መሠረት ምርጫና ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ለማስፈጸም የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ አንድ ላይ በመስማማት የአንድ ፓርቲ ፍላጎት እንደ ህዝብ ፍላጎት በማስመሰል ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ለማስፈጸም እየሄደ ያለበት ርቀት በሀገርቱ ህግና ሥርዓትን የሚደፈጥጥ፣ ዴሞክራሲን የሚገድል፣ የህዝቦች ህገ መንግስታዊ መብት የሚቃረን መሆኑን ተመልክተናል።

ስለሆነም ፓርቲያችን ከዚህ በታች ያለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

  1. በአንድ ፓርቲ ገዥና ጠቅላይነት በህዝባችን ላይ ካለፍላጎቱ የሚደረገውን ክላስተር የሚባለውን አወቃቀር በጽኑ እናወግዛለን።

2.የህዝብ ጥያቄ በህዝበ ውሳኔ መቋጨት እንዳለበት ብናምንም የዎላይታ ብሄራዊ ክልል/ብቻዬን ክልል ልሁን/ የሚል ምርጫ ያልተካተተበት ህዝበ ውሳኔ የህዝቦች ፍላጎት ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔ በመሆኑ ዘላቂ ሰላምና መተማመንን የማይፈጥርና ህዝቦች እርስ በርስ በጎሪጥ እንድተያዩ የሚያደርግ እንዲሁም አንዳቸው ሌላውን በስጋት የሚመለከቱበት በመሆኑ በጽኑ እንቃወማለን።

  1. አሁን ህዝበ ውሳኔ ይደረጋል የተባለው የክላስተር አወቃቀር በሀገርቷ ሥራ ላይ ባለው ህገመንግስት በውል የማይታወቅና ህጋዊ እውቅና የለለው በመሆኑና የሀገርቷን ህገመንግስት የሚቃረን በመሆኑ ተፈጻሚነት የለለውና ህገወጥ አሠራር በመሆኑ የሀገርቷ ሀብት በከንቱ እንዳይባክን እናሳስባለን።
  2. የዎላይታ ህዝብ ራስን በራስ ለማስተዳደር ያቀረበውን ህገ መንግስታዊ መብት ጨፍልቆ የአንድ ፓርቲ ጠቅላይ ገዥነት ለማስፈን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እየወሰደ ያለውን ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄድ በአስቸኳይ አቁሞ የሀገርቱን የበላይ ህግ የሆነውን ህገ መንግስት እንድያከብር አጥብቀን እንጠይቃለን።

በመጨረሻም በህዝበ ውሳኔው የዎላይታ ብሄራዊ ክልል የሚል አማራጭ የለሌበትን ህዝባችንና ፓርቲያችን በጽኑ የሚቃወምና የማይቀበል እንዲሁም እውቅና የማይሰጥ መሆኑን እየገለጽን የህዝባችን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ እስክመለስ ድረስ የዎላይታ ህዝብ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንድቀጥል እናሳስባለን።

የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ዎሕዴግ
ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም
ዎላይታ ሶዶ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: