

የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለማስፈጸም ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው የመጡ የፈተና አስፈጻሚዎች በዛሬው ዕለት በዎላይታ ዞን የሚገኘውን ኡማ ሰው ሰራሽ ኃይቅን ጎብኝተዋል።
የግልገል ግቤ ቁጥር ሦስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መገንባትን ተከትሎ የተፈጠረው የኡማ ሰው ሰራሽ ኃይቅ በዓሳ ልማት መስክ ከፍተኛ ውጤት እየሰጠ ይገኛል።

ይህ ሰው ሰራሽ ኃይቅ ከዓሳ ልማት ስራ በተጨማሪ በዎላይታ እና ዳውሮ ዞን አዋሳኝ አካባቢ ላሉ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የውሀ ላይ ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጠ ነው።
በኡማ ወንዝ ላይ የተመሰረተው ይህ ዓይነ- ግቡ እና እጅግ ማራኪ ሰው ሰራሽ ኃይቅ ለአካባቢው የቱርስት መዳረሻ ሆኖ የበለጠ እንዲያገለግል ትኩረት ተሰጥቶት ሊለማ ይገባል ብለዋል ጎብኝዎቹ።
ስፍራውን በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር እና የበለጠ እንዲለማ በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረብ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
የፈተና አስፈጻሚዎቹ አክለውም፤ የኡማ ሰው ሰራሽ ኃይቅን በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን የላቀ ደስታ ገልጸዋል።

ይህን መሰሉ ጉብኝት ሀገሪቱ ያላትን የመስህብ ስፍራዎች ከማወቅ ባሻገር፤ የእርስ በርስ ትስስርን እና ሀገራዊ አንድነትን ያጠናክራል ብለዋል የፈተና አስፈጻሚዎቹ።
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የኡማ ሰው ሰራሽ ኃይቅ ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ በዓሳ ልማት መስክ ሠፊ ስራ ለመስራት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጿል።#wolaitatimes