
ገናና የዎላይታ ንጉስ ሞቶሎሚ ማናቸው?

በ12ኛው ክፍለ ዘመን አጥቢያ የዳሞት (አሁን ዎላይታ ከሚባለው አካባቢ) ሞቶሎሚ የሚባል ሀይለኛ ንጉስ ተነስቶ ከፍተኛ ጦር ይዞ ወደ ሸዋ መዝመት ጀመረ። መጀመሪያ የተጠቀመበት ዘዴ አሁን ሳይኮሎጂኪል ውጊያ የሚባለው። የፈራ ጠባ የማስደንገጫና ሕሊናን የማወኪያና የማደናበሪያ ጦር በማኪያሄድ ነው ወረራውን የጀመረው። ቀስ እያለ ግን ወታደሩን እያበራከተ ቡልጋንና ሳልልሽን ድል አድርጎ ያዘ። ሞቶሎሚ የያዘውን አገር ከጭፍጨፋ የተረፈውን ሕዝብ የማይችለው ግብር እየጣለበት የስቃይ ዘመን ጀመረ። ከቡልጋ ቀጥሎ ግዛቱን በማስፋፋት ደዋሮንና ደቡብ ሸዋን ድምጥማጡን አጠፋው።

ሞቶሎሚ ያገኛቸውን አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ሁሉ አቃጥሎና ካህናቱን ፈጅቶ የሸዋ ህዝብን እሱ ያመጣውን እምነት እንዲከተል አስገደደ። ዘመኑ የዛጉዌ ስለ ነበርና ያካባቢው ሕዝብ ሞቶሎሚን መቋቋም አለመቻሉን ለዛጎዌው ንጉስ የአድኑንና የድረሱልን መልእክት ቢላክለትም አቅም ስላልነበረው ምንም ሊያደርግ አልቻለም። ነገር ግን ሞቶሎሚ ሰሜን እስከ ጫጫና ወገጪት ወንዝ ድረስ እየዘለቀ ስለ መጣና ግብርም ስለ ከለከለ የዛጎዌው ንጉስ ዜና ጴጥሮስ ከፍተኛ ሰራዊት አሰባስቦ በብዙ ታቦቶችና ካህናት ታጅቦ ሞተሎሚን ጦር ገጠመው። ነገር ግን ድል የመተሎሚ ሆኖ ዜና ጴጥሮስ ሳይቀር በጦርነቱ ሞተ። ሞቶሎሚም ራሱን ቆርጦ አገር ላገር ካሳየ በኋላ ራስ ቅሉን የእህል መስፈሪያ አደረገው። ሞቶሎሚ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ለመያዝ የሚያስችል ጉልበት ነበረው።
በዚህ ዘመን ግን ከፍተኛ የክርስትና መምህር የነበሩት አቡነ ተክለ ኃይማኖት ክርስቲያኑን በማስተባበር ከፍተኛ ሀይል አስነስተው የሞቶሎሚን ጦር አስከበቡት። ጦርነት ከመነሳቱ በፊት ግን አቡዬ መተሎሚን እንዲያነጋግራቸው ጠይቀውት ፣ እሱም ፈቃደኛ በመሆኑ ወደሱ ገቡ። ብዙ ተወያይተውም ንግግራቸው ሲያልቅ እሱም የክርስትና ሀይማኖት ተቀብሎ ወደመጣበት ዳሞት ሀይማኖቱን ይዞ ሄዶ የዳሞት ወይም የዎላይታ ሀይማኖት ክርስትና እዲሆን አደረገ። በታሪክ ተመራማሪ ዶክተር አበበ ሀረገወይን

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
Great keep it up.