ሁለት ህፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ
በጎፋ ዞን አቃቤ ህግ መምሪያ ልዩ ልዩ የወንጀል ጉዳዮች ሥራ ሂደት ዋና አስተባባሪ አቶ ምስራቅ በላቸው እንደገለጹት ለህጻናቱ ህይወት ህልፈት በፖሊስ የወንጀል ምርመራ በመረጋገጡ ነው የፍርድ ውሳኔ የተላለፈው፡፡
በዞኑ ኡባ ደብረ ፀሀይ ወረዳ ጋዶላ ጎዱማ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ተከሳሽ አሳሼ አታረ የስድስትና የስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሁለት የወንድሙ ልጆችን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ረቡዕ ዕለት በግምት ከቀኑ 11 ሰዓት አከባቢ ሲሆን በእርሻ ማሳዬ የሚገኘውን አትክልት በበግ አስበልተዋል በሚል ሰበብ መሆኑን አንስተዋል።
ተከሳሹ ሁለቱን ህጻናት አባብሎ ወደ ቤቱ አስገብቶ በስለት ወግቶና ቆራርጦ በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለ በኋላ በማዳበሪያ ጠቅልሎ ሽንት ቤት ውስጥ መጣሉንም አስረድተዋል።
የዞኑ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አለሙ መለሰ እንደገለጹት ወንጀሉን የፈጸመው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሆኖ የጎፋ ዞን አቃቤ ህግም የወንጀል ህግ አንቀፅ 539(1)ሀ/ድንጋጌን በመጥቀስ ክስ መስርቶበት በማስረጃ በመረጋገጡ ግለሰቡ በእስራት እንዲቀጣ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት የጎፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዳር 15/2015 ዓ.ም በዋለው የወንጀል ችሎት በተከሳሽ አቶ አሳሼ አታረ ላይ የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ውሳኔ መተላለፉን ዳኛው ተናግረዋል።
ወንጀለኞች የሚቀጡት ለራሳቸው እንዲታረሙና ሌሎች እንዲማሩበት መሆኑን የገለፁት የአቃቤ ህግ ባለሙያ አቶ መንግስቱ ግሩም ህብረተሰቡ ከወንጀል ነክ ድርጊቶች እንዲቆጠቡና ልማት ላይ እንዲረባረቡ አሳስበዋል።ደሬቴድ

