የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በአከባቢው በደረሰው ጫና ምክኒያት ላልተወሰነ ጊዜ ስለመዘጋቱ ስለመግለጽ ይሆናል🙏

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከኢትዮጲያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሚዲያ ስራ በሕጋዊነት ለመስራት ከጀመረ ወዲህ በተለይም በአካባቢው አማራጭ የሚዲያ አገልግሎት ለመስጠት መረጃ የማግኘትና የማሰራጨት ነፃነት በብዙ ፈተናዎች በገባበት ሁኔታ ላይም በተቻለ መጠን መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ስያደርግ ቆይቷል፡፡

ከዚህ በፊት የሚዲያው መስራች ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የሚዲያ ህግ ባከበረ መንገድ ለሕብረተሰቡ የተለያዩ ተጨባጭ መረጃዎችን በማድረሱ በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ከየትኛውም ተቋም ድጋፍና ለሚዲያ አገልግሎት ከዞንና ክልል መረጃ እንዳይሰጥ በመከልከሉ ቅሬታ ለሚመለከታቸው አካላት ብናቀርብም ምላሽ አልተሰጠም፡፡

በአሁኑ ወቅት ከቀን 19/03/2015 ዓ.ም ጀምሮ የሚዲያ መስራችና ባለቤት ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ በመንግስት ላይ ጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል በሚል ተጠርጥሮ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ከቆየበት በትናንትናው ዕለት 28/03/2015 ዓ.ም በ30 ሺህ ብር ዋስትና ተለቋል፡፡ ተመሳሳይ ጫና በመኖሩ ሌሎች የሚዲያው ጋዜጠኞችም ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው በመሆኑ ቢሮ ተዘግቷል፡፡

በመሆኑም ሚዲያው በክልልና በዞኑ እንደ ህጋዊ ሚዲያ ለመስራት የሚያስችል መረጃ የማግኘት ነጻነት፣ የጋዜጠኞች የአካል ነጻነት፣ መረጃ የማግኘት፣ በተለያዩ መድረኮችና ስብሰባዎች ላይ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ከቦታው ለማድረስ የመገኘትና ድጋፍ የማግኘት መብት፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፤ በዞኑና በክልሉ መንግስት በተደራጀ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ ላልተወሰነ ጊዜ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ለህብረተሰቡ እውነትን መሰረት ያደረጉ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለማድረስ ተደራጅቶ እስኪመለስ በትዕግስት እንድትጠብቁ በትህትና እናሳውቃለን፡፡

በተጨማሪም በአከባቢው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማንሳትና መጠየቅ፣ የመንግስት አሰራር ክፍተቶችን መናገርና መተቸት “እንደ ጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ህዝብን በመንግስት ላይ ማነሳሳት በሚል” በፀጥታ መዋቅርና ፍርድ ቤቶች ላይ ጫና በማድረግ ከህግ አካሄድ ውጪ ወደ የሚያሳስርበት ደረጃ በመድረሱና እንደ ሌሎች ኢትዮጵያ አከባቢ የፖለቲካ ልዩነት ሀሳብ ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት በህዝብ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ የመወያየት ሆነ ሀሳብ የመግለፅና የመወሰን ሁኔታ ዝግ በመሆኑ እንዲሁም በአከባቢው ከዚህ በፊት በክልል አደረጃጀት ምክንያት ተከስቶ በነበረው ቅሬታና አለመግባባት በበቂ ህዝብ ውይይትና ምክክር መግባባት ሳይደረስበት የሚያካሄደው ህዝበ ውሳኔ አካሄድ ዙሪያም ሚዲያው አማራጭ የሀሳብ ልዩነት ያላቸውን ህብረተሰብ ክፍሎችን በተመለከተ ዘገባ ለመስራት የመረጃ ነጻነት በአከባቢው ባለመኖሩና በሰላማዊ መንገድ አማራጭ የሀሳብ ልዩነት የሚያራምዱ የዩንቨርስቲ ሆነ የፓለቲካ አመራሮችን፣ ባለሙያዎችን፣ ባለሀብቶችን እና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የህዝብ ወገንተኝነት ያላቸውን ከስራ ማባረር፣ ማግለል፣ ማሰር፣ መሳደድ እንዲሁም ሰበዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የመጣስ ድርጊቶች በአከባቢው መንግስት አመራሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛና እየከፋ መምጣቱንም ጭምር ለፈደራል መንግስትና ለአለም ለማሳየትና ለማሰማት ማሳያ እንዲሆን ላልተወሰነ ጊዜ የሚዲያው አገልግሎት ለማቆም መገደዳችንንም እናሳውቃለን፡፡

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ኤዲቶሪያል ቦርድ
ታህሳስ 01/2015 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: