wt-ofce-at-sodo

ሚዲያ ከነገ ጀምሮ መደበኛ አገልግሎት መስጠት ይጀመራል።

በአከባቢው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማንሳትና መጠየቅ፣ የመንግስት አሰራር ክፍተቶችን መናገርና መተቸት “እንደ ጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ህዝብን በመንግስት ላይ ማነሳሳት በሚል” በፀጥታ መዋቅርና ፍርድ ቤቶች ላይ ጫና በማድረግ ከህግ አካሄድ ውጪ በተደጋጋሚ የሚያሳስርበት ደረጃ በመድረሱ ሚዲያው ዋና መቀመጫ የሆነው ዎላይታ ሶዶ ቢሮ ተዘግቶ መደበኛ ስራውን ከነገ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ውጪ ሆኖ ከስደት ሀገር ለመስራት ተገዷል።

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከኢትዮጲያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሚዲያ ስራ በሕጋዊነት ለመስራት የሚያስችል ፈቃድ ያለው ቢሆንም አማራጭ የሀሳብ ልዩነት ያላቸውን ህብረተሰብ ክፍሎችን በተመለከተ ዘገባ ለመስራት መረጃ የማግኘት መብትና ነጻነት በአከባቢው ባለመኖሩና በተጨማርም በሰላማዊ መንገድ አማራጭ የሀሳብ ልዩነት የሚያራምዱ የዩንቨርስቲ ሆነ የፓለቲካ አመራሮችን፣ ባለሙያዎችን፣ ባለሀብቶችን እና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የህዝብ ወገንተኝነት ያላቸውን ከስራ ማባረር፣ ማግለል፣ ማሰር፣ መሳደድ እንዲሁም ሰበዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የመጣስ ድርጊቶች በአከባቢው መንግስት አመራሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛና እየከፋ መምጣቱንም ጭምር ለፈደራል መንግስትና ለአለም ለማሳየትና ለማሰማት ማሳያ እንዲሆን በሚል ገልፀን ለሳምንት ያህል የሚዲያው አገልግሎት ማቆማችንም ይታወሳል።

የሚዲያው መስራች ጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የሚዲያ ህግ ባከበረ መንገድ ለሕብረተሰቡ የተለያዩ ተጨባጭ መረጃዎችን በማድረሱ ብቻ በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ከየትኛውም ተቋም ድጋፍና ለሚዲያ አገልግሎት ከዞንና ክልል መረጃ እንዳይሰጥ በመከልከሉ ቅሬታ ለሚመለከታቸው አካላት ብናቀርብም ምላሽ ያልተሰጠ ሲሆን ባለፈው ሳምንትም በድጋሚ ጋዜጠኛ ናትናኤል በመንግስት ላይ ጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል በሚል ተጠርጥሮ በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ከቆየበት ከእስር ከተለቀቀ በኃላ ከሀገር ለመሰደድ ተገዷል። ተመሳሳይ ጫና በመኖሩ ሌሎች የሚዲያው ጋዜጠኞችም ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው በመሆኑ ቢሮ ተዘግቷል፡፡

በመሆኑም በአከባቢው ሆኖ ሚዲያው በነፃነት የመስራትና የፖለቲካ ልዩነት ሀሳብ ያላቸው ግለሰቦችና ተቋማት በህዝብ ጉዳይ ላይ የማወያየት ሆነ ሀሳብ እንዲገልፁ ዘገባ የመስራት ሁኔታ ዝግ መሆኑንና ጫና መድረሱ ተሳቢ ተደርገው የአከባቢው ጉዳዮች በሚዲያ በተለያዩ መንገዶች በነፃነት ለመስራት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን እንገልፃለን።

ለህብረተሰቡ ጠቃሚና ቅርበት ያላቸው መረጃዎችን በተዘረጋው የመረጃ ልውውጥ አሰራር የተለያዩ ውይይት መድረኮችን በመፍጠር፣ በቀጥታ ስርጭት፣ በስልክና የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም መረጃዎችን ከህብረተሰብ ክፍሎች በማግኘት ከወትሮው በተለየ መንገድ የሚዲያ አገልግሎት እንደምንሰጥም እናረጋግጣለን።

ሚዲያው እንደ ህጋዊ ሚዲያ ተቋም ለመስራት የሚያስችል መረጃ የማግኘት ነጻነት፣ የጋዜጠኞች የአካል ነጻነት፣ መረጃ የማግኘት፣ በተለያዩ መድረኮችና ስብሰባዎች ላይ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ ከቦታው ለማድረስ የመገኘትና ድጋፍ የማግኘት መብት፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፤ በዞኑና በክልሉ መንግስት በተደራጀ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ የሚዲያ አገልግሎትን ከኢትዮጵያ ውጪ ከሌላ ሀገር ለህብረተሰቡ እውነትን መሰረት ያደረጉ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ከነገ ጀምሮ ከወትሮው በተለየ አሰራር በፍፁም ገለልተኝነት ለማድረስ የተዘጋጀ መሆኑን እየገለፅን ተጨማሪ ሚዲያው የህዝብ ድምፅ እንዲሆን ትኩረት አቅጣጫ እንዲህ መሆን አለበት የምትሉትን ሀሳብ እንድትሰጡበት በትህትና እንጠይቃለን።

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ኤዲቶሪያል ቦርድ
ታህሳስ 10/2015 ዓ.ም