
“ከህጋዊ አሰራር ውጪ ህዝብን ለማፈን በጥቂት ግለሰቦች ተወስኖ የሚካሄደው ህዝቤ ውሳኔ” እንዳይካሄድና ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ይዞ ለመሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለፀ።

በቀድሞ ደቡብ ክልል ስር የነበሩ ስድስት ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች በጋራ ክልል እንደራጅ በሚለው ይካሄዳል የተባለው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ የህዝብ ፍላጎት ያልተካተተበትና ህጋዊ መሠረት የለለው በሚል የተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎችና ተቋማት በይፋ ለሚመለከታቸው አካላት ቅሬታ ቢያቀርቡም ምላሽ አለመሰጠቱን ዎህዴግ በላከልን መግለጫ ጨምሮ አሳውቋል።
ህዝበ ውሳኔው ሀገሪቱ የሚትመራበት ህገመንግስት የማያውቀው ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ከዚህ በፊት በህጋዊ መንገድ የዎላይታ ህዝብ በክልል እንደራጅ በሚል በየደረጃው ባለው ምክርቤቶች በሙሉ ድምፅ አፅድቆ የክልሉ ምክርቤት ምላሽ ባለመስጠቱ ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት ጥያቄው ቀርቦ ባለበት በኃይል ያንን ህዝባዊ መብት ጥያቄ በመሰረዝ ጥቂት ግለሰቦች ከህዝብ ክፍላት ውጪ እንዲቀለበስ መደረጉ ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ በመሆኑ ተቀባይነት አለመኖሩም ተገልጿል።
ዎህዴግ ባወጣው መግለጫ “ህዝብ ጥያቄ በህዝበ ውሳኔ መቋጨት እንዳለበት ብናምንም የዎላይታ ብሄራዊ ክልል/ብቻዬን ክልል ልሁን/ የሚል ምርጫ ያልተካተተበት ህዝበ ውሳኔ የህዝቦች ፍላጎት ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔ በመሆኑ ዘላቂ ሰላምና መተማመንን የማይፈጥርና ህዝቦች እርስ በርስ በጎሪጥ እንድተያዩ የሚያደርግ እንዲሁም አንዳቸው ሌላውን በስጋት የሚመለከቱበት በመሆኑ በጽኑ እንቃወማለን” ብሏል።
“አሁን ህዝበ ውሳኔ ይደረጋል የተባለው የክላስተር አወቃቀር በሀገርቷ ሥራ ላይ ባለው ህገመንግስት በውል የማይታወቅና ህጋዊ እውቅና የለለው በመሆኑና የሀገርቷን ህገመንግስት የሚቃረን በመሆኑ ተፈጻሚነት የለለውና ህገወጥ አሠራር በመሆኑ የሀገርቷ ሀብት በከንቱ እንዳይባክን እያሳሰብን በህዝበ ውሳኔው የዎላይታ ብሄራዊ ክልል የሚል አማራጭ የለሌበትን ህዝባችንና ፓርቲያችን በጽኑ የሚቃወምና የማይቀበል እንዲሁም እውቅና የማይሰጥ መሆኑን እየገለጽን የህዝባችን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ እስክመለስ ድረስ የዎላይታ ህዝብ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንቀጥላለን” ስልም የወጣው መግለጫ ያትታል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አዲሱ ክልል በተባለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚካተቱ ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ገድኦ፣ ኮንሶ ዞኖችንና አሌ፣ ቡርጂ፣ አማሮ ኬሌ፣ ባስኬቶ፣ ልዩ ወረዳዎችን አንድ ላይ ጨፍልቆ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል ክልል ውስጥ ለማደራጀት በብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ መሠረት ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ህዝበ ውሳኔ ላይ አምባገነንነት የታከለበት በመሆኑ እንደሚያወግዝ አብራርተዋል መግለጫው።
የዎላይታ ህዝብ ከሶስት አመት በፊት ከቀበሌ ድረስ በወረደ አካታች የህዝብ ውይይት በተወሰነ ውሳኔ በምክር ቤት ተወካዮቹ አማካኝነት የክልል እንሁን ጥያቄውን እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ መላኩ ይታወሳል። ዎላይታ ዞን ምክር ቤት ህገ መንግስት በሚፈቅደው አካሄድ በ2012 ዓ.ም ይግባኝ የጠየቀውን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ያለ ህዝብ ፍላጎት የሻረው ምክር ቤት የስልጣን ጊዜ የጨረሱ መሆናቸውንና ዎላይታ ሕዝብን መወከል የማይችሉ መሆናቸውንና በነዚህ ሰዎች የተወሰነ ውሳኔ ህዝብን እንደማይወክልም ግንባሩ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ህዝበ ውሳኔ ማለት የፖለቲካ ጥያቄውን ሁሉም አማራጮች ተቀምጦበት ህዝቡ በድምፅ የሚያፀድቅበት ወይም የሚያፈርስበት የተለየ ህጋዊ መንገድ ሆኖ በተወካዩ ድምጽ ከሚወሰንበት ጉዳይ ጋር ተቃራኒ መሆኑና ደግሞም ሕዝበ ውሳኔ ማለት አንድ የተለየ አከራካሪ ለሆነው ዓላማ ላይ ህዝቡ በአብላጫ ድምፅ የማጽደቅ ወይም ውድቅ ለማድረግ የመራጮች ሥልጣን ነው፣ መራጩ ሕዝብ ሊመርጥ ያሰበው ሁለትና ከዛ በላይ አከራካሪ ጉዳይ አማራጭ ሆኖ በግልጽ አስካልተቀመጠ ድረስ ህዝበ ውሳኔ ትርጉም አለመኖሩንም ግንባሩ በመግለጫው ገልጿል።
ነገር ግን በፌዴሬሽን ም/ቤት በኩል ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም እንዲከናወን ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ሁለት አማራጭ በፍጹም የሕዝብ ጥያቄ አማራጭ ሆኖ ካልቀረበ በስተቀር የህዝብ ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ማስመሰል ፖለቲካዊ አካሄድ ትውልድን የፖለቲካ ጥያቄ ወደ ቀጣይ ትውልድ ያሸጋገረ የህዝብ ጥያቄ የማይመልስ ቸልተኝነት የተካለበት የህዝብን የማስታወስ አቅም መናቅ፣ አለአግባብ የመንግስትን ሃብት ማባከን እና የተከፈለውን የትግሉ ሰማዕታት ነፍስ ላይ መቀለድ መሆኑንም ዎህዴግ ሁኔታውን አብራርቷል።
የሀገርቱ ህዝብ መብት ለማስፈጸም በህገ መንግስት መርሆችን ተከትሎ እንዲያሰፈጽም የተቋቋመው ፌዴረሽን ምክር ቤት እና በህግና በህዝብ ፍላጎት መሠረት ምርጫና ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ለማስፈጸም የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ አንድ ላይ በመስማማት የአንድ ፓርቲ ፍላጎት እንደ ህዝብ ፍላጎት በማስመሰል ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ለማስፈጸም እየሄደ ያለበት ርቀት በሀገርቱ ህግና ሥርዓትን የሚደፈጥጥ፣ ዴሞክራሲን የሚገድል፣ የህዝቦች ህገ መንግስታዊ መብት የሚቃረን መሆኑን ተመልክተናል ስልም ዎህዴግ በመግለጫው አሳውቋል።
በህዝበ ውሳኔው የዎላይታ ብሄራዊ ክልል የሚል አማራጭ የለሌበትን ህዝባችንና ፓርቲያችን በጽኑ የሚቃወምና የማይቀበል እንዲሁም እውቅና የማይሰጥ መሆኑን እየገለጽን የህዝባችን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ እስክመለስ ድረስ የዎላይታ ህዝብ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንድቀጥልም ግንባሩ ለህዝብ ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል ፓርቲው ከሌሎች አጋርሮች ጋር በመሆን “ከህጋዊ አሰራር ውጪ ህዝብን ለማፈን በጥቂት ግለሰቦች ተወስኖ በጉልበት የሚካሄደው ህዝቤ ውሳኔ እንዳይካሄድና ተፈፃሚነት እንዳይኖረው” ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ይዞ ለመሄድ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ከተላከልን መግለጫ ለማወቅ ችለናል።

