ባለፈው መስከረም የተፈጠረው ክስተት የቶላ እና ቤተሰቡን ሕይወት ያመሰቃቀለ ነበር።

በግብርና ሥራ የሚተዳደረው ቶላ ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ጃርዴጋ ጃርቴ በተሰኘ አካባቢ በሰላም ይኖር ነበር። አሁን ግን አዲስ አበባ ውስጥ የቀን ሥራ እየሠራ ቤተሰቦቹን ለደገፍ ይታትራል።

ቶላ በሚኖርበት ቀበሌ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ወንድሞቹን ጨምሮ ስምንት የቅርብ ዘመዶቹን አጥቷል።

እሱ እንደሚለው ጥቃቱን ያደረሱት ፋኖ የተሰኙ የታጣቂ ቡድን አባላት ሲሆን እሱ እና ቤተሰቦቹ ዒላማ የሆኑት ደግሞ “በብሔራቸው ምክንያት” ነው።

“ወንደሞቼ ሲገደሉ ልጆቻቸው እና ሚስቶቻቸው እየተመለከቱ ነበር። ውሃ ጠማን እያሉ እየለመኑ ነው የተገደሉት” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“አንደኛዋ ዘመዴ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች። አባቷ ሲገደል ወደ ሬሳው ሄዳ ‘እኔንም ግደሉኝ’ ስትል አለቀሰች። እሷንም በጭካኔ እዚያው ገደሏት።”

ራሱን እና ቤሰተቦቹን ለማዳን ሲል ከብቶቹን እና እርሻውን ጥሎ የተሰደደው ቶላ፣ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ የቀን ሥራ እየሠራ ቢኖርም የደረሰበትን መርሳት አልቻለም።

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ግድያ እና መፈናቀል የተለደመዱ የየቀን ክስተቶች ሆነዋል።

የአራት ልጆች አባት የሆነው ሐሰን ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ለዘመናት ኖሯል፤ ቤት ንብረት አፍርቷል፤ ወልዶ ስሟል።

አሁን ግን ልጆቹን እና ሚስቱን ይዞ ለዘመናት ከኖረበት ኪረሙ ከተሰኘው ቀበሌ ተፈናቅሎ በአቅራቢያው ካለ አንድ አነስተኛ ቀበሌ ተጠልሎ ይገኛል።

ሐሰን “በማንነታችን ምክንያት ደረሰብን” ባለው ጥቃት አጎቱን እና ሁለት የአጎቱን ልጆች በአንድ ቀን እንዳጣ ለቢቢሲ ይናገራል።

“ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ ዕድሜያቸው 90 የደረሱ አዛውንት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ታጣቂዎች መጥተው በፈጸሙት ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎች ናቸው የተገደሉት። ከጥቃቱ በመሸሽ ላይ የነበሩት የአጎቴ ልጆችም ተገድለውብኛል።”

ሐሰን እና ጎረቤቶቹ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በሕይወት የተረፉ ልጆቻቸውን ይዘው አሁን ስደትን ተያይዘውታል። “መንግሥት ደኅንነታችን ሊጠብቅ አልቻለም” ሲል የሚወቅሰው ሐሰን አብዛኛዎቹ ሕፃናት በረሃብ እያለቁ እንደሆነ ይናገራል።

ሐሰን፤ ኦነግ ሸኔ የተባለውን ታጣቂ ቡድን ለበርካታ ጥቃቶች ተጠያቂ ያደርጋል። አልፎም የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልሉ መንግሥት ለአደጋ አጋልጦ ሰጥቶናል ሲሉ ይወቅሳል።

ምዕራብ ኦሮሚያ በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት እረፍት አልባ ግጭት ውስጥ ይገኛል።

በተለይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በአብዛኛው የምዕራብ ኦሮሚያ ክፍል በመንግሥት ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል በሚደረግ ግጭት ሳቢያ ሰላማዊ ሰዎች ተጠቂ ሆነዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ በቆየው ጦርነት ምክንያት አንዳንዶች ‘የተረሳው ጦርነት’ ሲሉ የሚጠሩት የምዕራብ ኦሮሚያ ግጭት ከቅርብ ወራት ወዲህ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ የመጣ ይመስላል።

ሐሰንን ጨምሮ በርካታ አማራዎች የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነገ-ሸኔ) የተሰኘው ታጣቂ ቡድን ቢወቅሱም ቡድኑ ወቀሳዎችን በማጣጣል፣ ግድያዎቹ በገለልተኛ አካል ይጣሩ ሲል ይደመጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከወራት በፊት “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አደረሰው” ከተባለ አንድ ጥቃት በኋላ ቡድኑን ከአካባቢው ለማጥፋት ዝተው ነበር።

ቢሆንም ታጣቂው ቡድን በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት በበርካታ ቦታዎች ላይ ጥቃት የፈጸመ፣ የተጽእኖ ክልሉንም እያሰፋ መሆኑ እየተነገረ ነው።

“የምዕራብ ኦሮሚያው ግጭት የተረሳው አንደኛው በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ጦርነት ምክንያት ነው” ይላሉ የፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኟ ፀዳለ ለማ።

አዲስ ስታንዳርድ የተሰኘው ጋዜጣ መሥራች የሆኑት ፀዳለ በትግራይ ጦርነት ምክንያት ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ግጭት ሙሉ በሙሉ ተዘንግቷል የሚል እምነት አላቸው።

በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ‘አሸባሪ ቡድን’ ተብሎ የተሰየመው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፤ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተለይቶ የወጣ ቡድን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ ከአገር ውጪ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ ጥሪ ሲያቀርቡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ጥሪውን ተቀብሎ ሲገባ፣ የቡድኑ ታጣቂ ክንፍ ከሆኑት መካከል ተለይተው በትጥቅ እንቅስቃሴው ቀጠሉበት።

በዚህ ወቅት ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጋር ደም አፋሳሽ ወደሆነ ጦርነት ለማምራት አንድ ሁለት እያሉ ነበር።

መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሰላማዊ ዜጎችን ሆን ብሎ ገድሏል ሲል በተደጋጋሚ ሲወቅስ፤ ታጣቂው ቡድን በበኩሉ የመንግሥት ወታደሮችን ለግድያው ተጠያቂ ናቸው ሲል ይከሳል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ባወጣቸው ዘገባዎች የኦሮሞ ነፃነት ጦርም ሆነ የመንግሥት ወታደሮች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ለደረሱ ግድያዎች ተጠያቂዎች ናቸው ይላል።

ገንዘብ የሚከፈልበት አፈና

መንግሥት ኦነግ ሸኔ ሲል የሚጠራው ቡድን ራሱን ለማደራጀት በሚል የባንክ ዘራፈዎች ከማካሄድ ባለፈ የመንግሥት ባለሥልጣናትንና ሌሎች ግለሰቦችን በማፈን የማስለቀቂያ ገንዘብ በመቀበል ይከሰሳል።

በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ ኦሮሚያ የተለያዩ ግለሰቦች በታጣቂው ቡድን ታፍነው ተወስደው የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው እንደተለቀቁ፤ አሁንም በርካቶች እየታፈኑ እንደሆነ ቢቢሲ ሰምቷል።

ነገር ግን አብዛኛዎቹ ግለሰቦች ይህንን ታሪካቸውን በግልጽ መናገር አይፈልጉም። ምክንያታቸው ደግሞ ታጣቂው ቡድን ይህን ጉዳይ ለሌሎች እንዳይናገሩ አስጠንቅቆ ስለለቀቃቸው ኋላ የሚፈጠረውን አደጋ በመስጋት ነው።

በቅርቡ ከአንድ ደርዘን በላይ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሠራተኞች ታፍነው የማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው እንደተለቀቁ በቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።

ይህ ክስተት ኅዳር 21 የተሰከተ ሲሆን 17 የፋብሪካው ሠራተኞች በነፍስ ወከፍ ከ300 እስከ 500 ሺህ ብር ከፍለው እንደተለቀቁ ተነግሯል።

የናይጄሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ ንብረት የሆነው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ስለሁኔታው ክስተቱ የሰጠው አስተያየት የለም።

መሰል አፈናዎችን ጨምሮ በርካታ ግድያዎች መፈናቀሎች የሚስተዋሉበት የምዕራብ ኦሮሚያ ግጭት ከመንግሥት እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ተነፍጎታል ሲሉ ብዙዎች አስተያየት ይሰጣሉ።

በግጭቱ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱ ሰላማዊ ነዋሪዎች አሁን በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች አካባቢዎች ተጠልለው ይገኛሉ።

አልፎም አንዳንድ የጥቃት ሰለባዎች ባለፉት ጥቂት ወራት ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

በርካታ ሕፃናት ከትምህርት ገበታቸው ተነጥለዋል፤ ረዥም ጊዜ የሚቆይ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በመድኃኒት እጦት እየተሰቃዩ ነው።

ቢቢሲ ያናገራቸው አብዛኞቹ ተፈናቃዮች መንግሥት ሰላም ወዳለበት ቦታ ወስዶ እንዲያሰፍራቸውና የእለት ደራሽ ድጋፍ እንዲያቀርብላቸው ይማፀናሉ።

“ከመንግሥት የምንሻው ነገር አሁን ካለንበት ቦታ እንዲያስነሳን እና ሰላም ወደላበት እንዲያፍረን ነው” ይላል ሐሰን ሳግ እየተናነቀው። በዚህ ዘገባ ላይ የተካተቱ ግለሰቦች ስም ለደኅንነታቸው ሲባል ተቀይሯል ስል ቢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: