በክልሉ ባለፈው ዓመት በበልግ ወቅት በተከሰተው የዝናብ መዛባት ምክንያት 3 ሚሊዮን 479 ሺህ 270 የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ ክፍተት መጋለጣቸውን የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቋል።

ዎላይታ ዞን ቆላማ ወረዳዎች እና ማዕከላዊ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ስምጥ ሸለቆ ወረዳዎች፣ ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ፣ አሌ ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች፣ ጎፋ ዞን፣ ጋሞ ዞን ቆላማ ወረዳዎች ላይ የበልግ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን በግምገማው ማስቀመጡን አቶ ጋንታ አብራርተዋል።

ከእነዚህ ለምግብ ክፍተት ከተጋለጡት እና ድጋፍ ሊደርሳቸው ይገባል ተብለው ከተለዩት ውስጥ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በአስቸኳይ ድጋፉ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምኣ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ገልጸዋል።

ራሳቸውን መመገብ ለማይችሉ በመንግስት፣ በህብረተሰቡ እና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከመስከረም ወር ጀምሮ በቂ ባይሆንም ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በቀጣይም ድጋፍን ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባሉት የበልግ እና የመኸር ቅድመ ምርት ግምገማ ከፌደራል ፣ ከክልል እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት የተውጣጣ ቡድን ሐምሌ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው የበልግ ወቅት ቅድመ ምርት ግምገማ 3 ሚሊዮን 479 ሺህ 270 የሚጠጉ ሰዎች ለምግብ ክፍተት እንደሚጋለጡ ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

በዚህም ጉዳዩ ለክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት ቀርቦ በተለይ በቆላማ አካባቢዎች ደቡብ ኦሞ፣ ኮንሶ፣ አሌ ደራሼ፣ አማሮ፣ ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች፣ ጎፋ ዞን፣ ጋሞ ዞን ቆላማ ወረዳዎች፣ ዎላይታ ዞን ቆላማ ወረዳዎች እና ማዕከላዊ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ስምጥ ሸለቆ ወረዳዎች ላይ የበልግ ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን በግምገማው ማስቀመጡን አቶ ጋንታ አብራርተዋል።

የክልሉ መንግስት እነዚህን ወገኖች ተደራሽ ለማድረግ በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲው መሰረት ህብረተሰቡን በማስተባበር፣ ባሉት የተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች እና ድጋፍ የሚሰጡ አካላት በጋራ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጡ ውሳኔ መተላለፉን ገልጸዋል።

የክልሉ መንግስት አደጋ ጊዜ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋሚያ ፈንድ አካውንት ተከፍቶ ድጋፍ እየተሰባሰበ መሆኑን አክለዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች በተደረገው የመኸር ቅድመ ምርት ግምገማም ጉዳቱ እንዳለ የተገመገመ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ ሪፖርቱ በክልሉ መንግስት ተገምግሞ የሚጠቃለል እንደሚሆንም ተገልጿል።

ይህም በቀጣይ ከጥር ወር ጀምሮ የሚወሰዱ እርምጃዎች እና ለተጎጂዎች የሚደርሱ ድጋፎች በምን አይነት መልኩ እንደሚቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚሰጡበት ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በክልሉ ላለፉት አራት ዓመታት በተከሰተው የዝናብ መዛባት የተከሰተውን የምግብ ክፍተት ለማሻሻል የግብርና ስራዎችን በተለየ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ አቶ ጋንታ ተናግረዋል።

በሚቀጥለው በልግ በፍጥነት የሚደርሱ ሰብሎችን በመዝራት ፣ ማታ ላይ እርጥበትን በማቆር፣ በተለይ እርጥበት አጠር በሆኑ ቦታዎች ላይ ቀጣይነት ያለው ውሃን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል ስል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: