
ለሪፈረንደሙ ምርጫ ካርድ ከየቤተ እምነቶች ለሚወጡ ሰዎች ለመስጠት የተደረገው ሙከራ በዎላይታ ተቃውሞ መግጠሙ ተነገረ።

ይካሄዳል በተባለው ሕዝበ ውሳኔ ላይ ላለመሳተፍ በርካቶች የምርጫ ካርድ ባለመውሰድ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከመግለፁ የተነሳ የሕዝበ ውሳኔው ምዝገባ ከሚደረግበት የምርጫ ጣቢያ በመውጣት ወደየቤተ እምነቶች በማቅናት በዛሬው ማለዳ ለሚገቡ ምዕመናን በር ላይ ለማደል ቢሞክሩም ሕዝባዊ ተቋውሞ መግጠሙን ከስፍራው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ባለፈው የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር( ዎህዴግ) እና የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ባወጡት መግለጫ እንዳመላከቱት የፖለቲካ ውሳኔ ተከትሎ ወደ ትግበራ የገባው ኢሕገመንግስታዊ ሕዝበ ውሳኔ ተብሎ ተቃውሞ እየገጠመው መቆየቱ ይታወቃል።
“የዎላይታ ሕዝብ ሕገመንግስታዊ መብቱን በመነጠቁ በጥቂት ፖለቲከኞች የተሰናዳውን ኢሕገመንግስታዊ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ላለመሳተፍ የምርጫ ካርድ ባለመውሰድ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ከመግለፁ የተነሳ የምርጫ ቦርድ ያለ ሕግ አግባብ የሕዝበ ውሳኔው ምዝገባ ከሚደረግበት የምርጫ ጣቢያ በመውጣት ቤተክርስቲያን በማቅናት ዛሬ ማለዳ ቤተክርስቲያን ለሚገቡ ሰዎች በር ላይ ለማደል ቢሞክሩም ሕዝቡ ምርጫ ቦርድ በሕግ አግባብ በተሰጠው ምርጫ ጣቢያ እንጂ ቤተክርስቲያን የምርጫ ጣቢያ አይደለም በማለት ተቃውሞ አስነስቷል” ስል አንድ ሁኔታውን ከቦታው የተመለከተው የዎህዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል አስረድተዋል።
እንደ ስራ አስፈፃሚው ገለፃ መንግስት በፓርቲው በኩል ይደረጋል የተባለው ምርጫ የህዝብ ፍላጎት ያልተካተተበትና የሀገሪቱን ህገመንግስት በግልጽ የጣሳ አካሄድ ብሎ በህጋዊ መንገድ ለሚመለከታቸው አካላት አቤቱታ ቢቀርብም እስካሁን በእምቢተኝነት እየሄደ መሆኑን በመግለፅ ያለህዝብ ፍላጎት በግድ የሚጫን ነገር አላስፈላጊ ዋጋ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
እስካሁን ይካሄዳል ለተባለው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ወደ ምርጫ ጣቢያው ሄደው ካርድ የሚወስዱት አመራሮች፣ እንዲሁም በተለያዩ መንግስት ድጋፍ የሚተዳደሩ ግለሰቦችን ጥቅማቸው እንደሚቆም በማስፈራራት በግድ ካርድ እንዲወስዱ ጫና እየተደረገ ስለመሆኑና አብዘኛው ህብረተሰብ ክፍሎች ካርድ ባለመውሰድ እምቢተኝነት እያሳዩ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።

ባለፈው ቀን ዎህደግ “ከህጋዊ አሰራር ውጪ ህዝብን ለማፈን በጥቂት ግለሰቦች ተወስኖ የሚካሄደው ህዝቤ ውሳኔ” እንዳይካሄድና ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ይዞ ለመሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩ መግለጽ ይታወሳል።
በቀድሞ ደቡብ ክልል ስር የነበሩ ስድስት ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች በጋራ ክልል እንደራጅ በሚለው ይካሄዳል የተባለው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ የህዝብ ፍላጎት ያልተካተተበትና ህጋዊ መሠረት የለለው በሚል የተለያዩ ፓለቲካ ፓርቲዎችና ተቋማት በይፋ ለሚመለከታቸው አካላት ቅሬታ ቢያቀርቡም ምላሽ አለመሰጠቱን ዎህዴግ በላከልን መግለጫ ጨምሮ አሳውቀው ነበር።

ህዝበ ውሳኔው ሀገሪቱ የሚትመራበት ህገመንግስት የማያውቀው ብቻ ሳይሆን ለምሳሌ ከዚህ በፊት በህጋዊ መንገድ የዎላይታ ህዝብ በክልል እንደራጅ በሚል በየደረጃው ባለው ምክርቤቶች በሙሉ ድምፅ አፅድቆ የክልሉ ምክርቤት ምላሽ ባለመስጠቱ ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት ጥያቄው ቀርቦ ባለበት በኃይል ያንን ህዝባዊ መብት ጥያቄ በመሰረዝ ጥቂት ግለሰቦች ከህዝብ ክፍላት ውጪ እንዲቀለበስ መደረጉ ኢዴሞክራሲያዊ አካሄድ በመሆኑ ተቀባይነት አለመኖሩም ገልጿል።
ዎህዴግ ባወጣው መግለጫ “ህዝብ ጥያቄ በህዝበ ውሳኔ መቋጨት እንዳለበት ብናምንም የዎላይታ ብሄራዊ ክልል/ብቻዬን ክልል ልሁን/ የሚል ምርጫ ያልተካተተበት ህዝበ ውሳኔ የህዝቦች ፍላጎት ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔ በመሆኑ ዘላቂ ሰላምና መተማመንን የማይፈጥርና ህዝቦች እርስ በርስ በጎሪጥ እንድተያዩ የሚያደርግ እንዲሁም አንዳቸው ሌላውን በስጋት የሚመለከቱበት በመሆኑ በጽኑ እንቃወማለን” ብሏል።
“አሁን ህዝበ ውሳኔ ይደረጋል የተባለው የክላስተር አወቃቀር በሀገርቷ ሥራ ላይ ባለው ህገመንግስት በውል የማይታወቅና ህጋዊ እውቅና የለለው በመሆኑና የሀገርቷን ህገመንግስት የሚቃረን በመሆኑ ተፈጻሚነት የለለውና ህገወጥ አሠራር በመሆኑ የሀገርቷ ሀብት በከንቱ እንዳይባክን እያሳሰብን በህዝበ ውሳኔው የዎላይታ ብሄራዊ ክልል የሚል አማራጭ የለሌበትን ህዝባችንና ፓርቲያችን በጽኑ የሚቃወምና የማይቀበል እንዲሁም እውቅና የማይሰጥ መሆኑን እየገለጽን የህዝባችን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ እስክመለስ ድረስ የዎላይታ ህዝብ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንቀጥላለን” ስልም የወጣው መግለጫ ያትታል ስል መዘገባችን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አዲሱ ክልል በተባለው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚካተቱ ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ገድኦ፣ ኮንሶ ዞኖችንና አሌ፣ ቡርጂ፣ አማሮ ኬሌ፣ ባስኬቶ፣ ልዩ ወረዳዎችን አንድ ላይ ጨፍልቆ ደቡብ ኢትዮጵያ በሚል ክልል ውስጥ ለማደራጀት በብልጽግና ፓርቲ ውሳኔ መሠረት ከህዝብ ፍላጎት ውጭ ህዝበ ውሳኔ ላይ አምባገነንነት የታከለበት በመሆኑ እንደሚያወግዝ አብራርተዋል መግለጫው።
የዎላይታ ህዝብ ከሶስት አመት በፊት ከቀበሌ ድረስ በወረደ አካታች የህዝብ ውይይት በተወሰነ ውሳኔ በምክር ቤት ተወካዮቹ አማካኝነት የክልል እንሁን ጥያቄውን እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድረስ መላኩ ይታወሳል። ዎላይታ ዞን ምክር ቤት ህገ መንግስት በሚፈቅደው አካሄድ በ2012 ዓ.ም ይግባኝ የጠየቀውን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ያለ ህዝብ ፍላጎት የሻረው ምክር ቤት የስልጣን ጊዜ የጨረሱ መሆናቸውንና ዎላይታ ሕዝብን መወከል የማይችሉ መሆናቸውንና በነዚህ ሰዎች የተወሰነ ውሳኔ ህዝብን እንደማይወክልም ግንባሩ ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ህዝበ ውሳኔ ማለት የፖለቲካ ጥያቄውን ሁሉም አማራጮች ተቀምጦበት ህዝቡ በድምፅ የሚያፀድቅበት ወይም የሚያፈርስበት የተለየ ህጋዊ መንገድ ሆኖ በተወካዩ ድምጽ ከሚወሰንበት ጉዳይ ጋር ተቃራኒ መሆኑና ደግሞም ሕዝበ ውሳኔ ማለት አንድ የተለየ አከራካሪ ለሆነው ዓላማ ላይ ህዝቡ በአብላጫ ድምፅ የማጽደቅ ወይም ውድቅ ለማድረግ የመራጮች ሥልጣን ነው፣ መራጩ ሕዝብ ሊመርጥ ያሰበው ሁለትና ከዛ በላይ አከራካሪ ጉዳይ አማራጭ ሆኖ በግልጽ አስካልተቀመጠ ድረስ ህዝበ ውሳኔ ትርጉም አለመኖሩንም ግንባሩ በመግለጫው ገልጿል።
ነገር ግን በፌዴሬሽን ም/ቤት በኩል ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም እንዲከናወን ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ሁለት አማራጭ በፍጹም የሕዝብ ጥያቄ አማራጭ ሆኖ ካልቀረበ በስተቀር የህዝብ ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ማስመሰል ፖለቲካዊ አካሄድ ትውልድን የፖለቲካ ጥያቄ ወደ ቀጣይ ትውልድ ያሸጋገረ የህዝብ ጥያቄ የማይመልስ ቸልተኝነት የተካለበት የህዝብን የማስታወስ አቅም መናቅ፣ አለአግባብ የመንግስትን ሃብት ማባከን እና የተከፈለውን የትግሉ ሰማዕታት ነፍስ ላይ መቀለድ መሆኑንም ዎህዴግ ሁኔታውን አብራርቶ ነበር በመግለጫው።
ጨምሮም የሀገርቱ ህዝብ መብት ለማስፈጸም በህገ መንግስት መርሆችን ተከትሎ እንዲያሰፈጽም የተቋቋመው ፌዴረሽን ምክር ቤት እና በህግና በህዝብ ፍላጎት መሠረት ምርጫና ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ለማስፈጸም የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ አንድ ላይ በመስማማት የአንድ ፓርቲ ፍላጎት እንደ ህዝብ ፍላጎት በማስመሰል ህዝበ ውሳኔ/ሪፈረንደም ለማስፈጸም እየሄደ ያለበት ርቀት በሀገርቱ ህግና ሥርዓትን የሚደፈጥጥ፣ ዴሞክራሲን የሚገድል፣ የህዝቦች ህገ መንግስታዊ መብት የሚቃረን መሆኑን ተመልክተናል ስልም ዎህዴግ በመግለጫው አሳውቋል።
በህዝበ ውሳኔው የዎላይታ ብሄራዊ ክልል የሚል አማራጭ የለሌበትን ህዝባችንና ፓርቲያችን በጽኑ የሚቃወምና የማይቀበል እንዲሁም እውቅና የማይሰጥ መሆኑን እየገለጽን የህዝባችን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በህጋዊ መንገድ እስክመለስ ድረስ የዎላይታ ህዝብ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንድቀጥልም ግንባሩ ለህዝብ ጥሪ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ፓርቲው ከሌሎች አጋርሮች ጋር በመሆን ከህጋዊ አሰራር ውጪ ህዝብን ለማፈን በጥቂት ግለሰቦች ተወስኖ የሚካሄደው ህዝቤ ውሳኔ እንዳይካሄድና ተፈፃሚነት እንዳይኖረው ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ይዞ ለመሄድ እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ከመግለጫው ለማወቅ ችለናል ስል የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከሁለት ቀናት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።


