የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት የኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ያደረጉት ጥሪ ከዚህ በፊት ከነበሩ ጥሪዎች የተለየ አይደለም አለ።

“ኦነግ” መንግስት በሰላም ጥሪ የማድረግ ትክክለኛ ፍላጎት ካለው አለምአቀፍ እና ብሄራዊ የድርድር መንገዶች ሊጠቀም ይገባል ብሏል በመግለጫው።

በኢትዮጵያ የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሲደረግ የነበረው ጦርነት የሰላም መንገድ የጀመረ ቢሆንም በኦሮሚያ ያለው ጦርነት ግን እንደቀጠለ ነው።

በክልሉ ያለው ጦርነት በሰላም እንዲጠናቀቅ ብዙዎች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን በቅርቡ 21 የኦሮሞ ተቋማት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና መንግስት ሶስተኛ አካል በተገኘበት እንዲነጋገሩ ጥሪ አድረገዋል።

ጥሪውን ተከትሎ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ምላሽ የሰጡት የፌዴራል መንግስት ኮምኒኬሽን ሚንስትር ዴታ አቶ ከበደ ዴሲሳ በመንግሰት በኩል ያለን አቋም አልተቀየረም ብለዋል።

ባለስልጣኑ በትጥቅ ትግል ላይ ያለው አካል መሳሪያ አስቀምጦ መግባት ነው እንጂ የምንቀበለው የሶስተኛ ወገን ድርድር የለም ሲሉ ተናግረዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ በትናንትናው እለት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጨፌ ኦሮሚያ ተገኝተው ለሰራዊቱ ነው የተባለ መልእክት አስተላልፈዋል።

አቶ ሽመልስ “ታጥቆ ለሚንቀሳቀሰው ለኦነግ ሸኔ የእርቅ ጥሪ እናደርጋለን” ሲሉ ተሰምተዋል ።

አቶ ሽመልስ ይህንን ማለታቸውን ተከትሎ ሰራዊቱ በመግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።

ሰራዊቱ የተደረገው ጥሪ ተፈላጊውን ግልጽነት እና ፍሬ ነገር የሚጎለው በመሆኑ በኦሮሚያ ውስጥ የሰላም ሂደት በፍጥነት ለማስጀመር ተስፋ የሚሰጥ አይደለም ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥሪዎች ማድረጉን የገለፀው ሰራዊቱ የአሁኑ ጥሪ የተለየ አይለይም ብሏል።

ከዚህ በፊት በነበረው ላይ የተለየ የጨመረው ነገር የለም የሚለው መግለጫው እንደዚህ አይነቱ ጥሪ ተመሳሳይ እና ድግግሞሽ ነው ሲል ገልጾታል።

የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ የተፈጠረውን ግጭት አሳሳቢነት በማሳነስ ጉዳዩን ወደ የሀገር ውስጥ ሽምግልናዎች ለመውሰድ ሙከራ ላይ መሆኑን ያነሳው መግለጫው ይህን ደግሞ ሰራዊቱ ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበለው እና በተደጋጋሚ ውድቅ ማድረጉን አስታውሷል።

የድርድር ሂደቱ ለሰራዊቱ አመራሮች እና ተደራዳሪዎች አስፈላጊ የሎጂስቲክ እና የደህንነት ማረጋገጫ እንደሚያስፈልገውም አክሏል።

ከምንም ነገር በላይ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን ሶስተኛ አካል ሊታዘበው እንደሚገባ የገለፀው ሰራዊቱ ከዚያ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በአስመራ ካደረጉት የከሸፈ ስምምነት የተለየ አይሆንም ብሏል።

በመሆኑም ሰራዊቱ የሚደረግ የሰላም ጥሪ አለም አቀፍ 3ኛ አካላትን በአደራዳሪነት የሚቀበል መሆን የሚገባው መሆኑን አስቀምጧል።

ሰራዊቱ አክሎም የኦሮሚያ ክልል መንግስት አንድ ተደራዳሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሰራዊቱ ጋር የሚደረገውን ድርድሩ በመንግሥት በኩል ሊመራ የሚገባው የፌዴራል መንግሥቱ መሆን ይገባዋል ብሏል።

በተጨባጭ ሰራዊቱ እየተዋጋ ያለው ከፌዴራል መንግስት ሃይሎች ጋራ መሆኑን የገለፀው መግለጫው ድርድሩ በህግም ይሁን በአካሄዱ ከክልሉ ስልጣን በላይ ነው ሲል አክሏል።

በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ጥሪ ሰራዊቱን ኦነግ ሸኔ በሚል ስም መጥራታቸውን ያነሳው መግለጫው ምንም እንኳ በይዘት ላይ የተለየ ትርጓሜ ባይኖረውም ካለው ጥርጣሬ አንጻር መንግስት በምን መልኩ ሂደቱን ለመቋጨት እንደሚፈልግ ጥያቄ ያስነሳል ብሏል።

በመሆኑም መንግስት በኦሮሚያ ያለው ጦርነት ማስቆም የሚፈልግ ከሆነ በአለምአቀፍ እንዲሁ በአገር አቀፍ አሰራር ተቋማዊ እና ደረጃውን የጠበቀ ድርድር ለማድረግ መዘጋጀት ይገባዋል ብሏል ስል ኦሚነ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *