ሰበር ዜና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዎላይታ ዞን ሕዝበ ውሣኔ አፈጻጸምን አስመልክቶ ውሣኔ አሳለፈ

ቦርዱ በዞኑ በተፈፀመው ከባድ የህግ ጥሰት መኖሩን በማረጋገጡ ተጨማሪ ምርምራ እንዲካሄድ ውሳኔ አሳለፈ።

ምርጭ ቦርዱ ከደቂቃዎች በፊት በወጣው መግለጫ በዎላይታ ዞን የተደረገውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ የሂደቱን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሁኔታ የፈጠሩ፤ በምርጫ ሕጉና አግባብነት ባላቸው መመሪያዎች መሠረት እንደ ከባድ የአሠራር ጥሠት የሚቆጠሩ ተግባራት ቁጥራቸው ጥቂት በማይባል የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተፈጽመው በመገኘታቸው፤ የጥሰቶቹን ስፋት እና የሚሸፍኑዋቸውን ጣቢያዎች በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ምርመራ እንዲከወን አዟል፤ የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀም የመጨረሻውን ውሣኔ በጉዳዩ ላይ እንደሚሰጥም አሳውቋል።

በዞኑ የህዝበ ውሳኔ አፈፃፀም የታዩ ጥሠቶች ዝርዝር፦

I. የመራጮች መዝገብን በተመለከተ

  1. በመራጮች ምዝገባ ወቅት በመዝገቡ ላይ የሠፈረው የመራጮች ፊርማ በድምፅ መስጫ ቀን ከተፈረመው ፊርማቸው ጋር የተለያየ መሆን፣
  2. በምዝገባ ወቅት በጽሑፍ ፊርማ የተፈረመ በድምፅ መስጫ ቀን በጣት አሻራ የተፈረመ የመራጮች ዝርዝር በመዝገቦቹ ላይ መታየቱ፣
  3. በምዝገባ ወቅት በጣት አሻራ የተፈረመ በድምፅ መስጫ ቀን በጽሑፍ ፊርማ የተፈረመ የመራጮች ዝርዝር በመዝገቦች ላይ መታየቱ፣
  4. በመራጮች መዝገብ ላይ ለተመዘገቡ የተለያዩ መራጮች (በምዝገባ ወቅትም፣ በድምፅ መስጫ ቀንም) አንድ ዓይነት ፊርማ ተፈርሞ መገኘቱ፣
  5. በመራጮች መዝገብ ላይ ከሚጠበቀው በላይ ብዛት ያለው የጣት አሻራ ምልክት (በመራጮች ምዝገባ ወቅትና በድምፅ መስጫ ቀን) የተደረገ መሆኑ፣
  6. በመራጮች መዝገብ ላይ የመራጮቹ መረጃ ተሞልተው ፊርማቸው በጽሑፍም ሆነ በአሻራ አለመሥፈሩ፣
  7. ከ18-50 ዕድሜ ያላቸውና ማንበብና መጻፍ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ በርካታ መራጮች በአሻራ እንደፈረሙ መታየቱ፣
  8. በመራጮች ምዝገባ ቀን በአሻራ ተፈርሞ በድምፅ መስጫ ቀን ፊርማ መፈረም ባለበት ቦታ ላይ የራይት ምልክት መደረጉ፣
  9. በመራጮች መዝገብ ላይ ስለመራጮቹ ሊሠፍሩ የሚገቡ የመራጮች መረጃ በአግባቡ አለመሞላታቸው፤

II. የድምፅ አሰጣጥና ውጤትን በተመለከተ

  1. ጥርጣሬን በሚፈጥር ሁኔታ በበርካታ ጣቢያዎች በመራጭነት የተመዘገቡና በሕዝበ ውሣኔው ቀን የመረጡ የመራጮች ብዛት ዕኩል ሆኖ መታየት፣
  2. የውጤት ማሳወቂያ ቅጽ ላይ የማይፈቀዱ የዕርምት ሥራዎች መሠራቱና በሠነዶቹ ላይ ከፍተኛ ሥርዝ ድልዝ መታየቱ፣
  3. የድምፅ መስጫ ወረቀት ብዛት፤ ከተመዘገቡና ድምፅ ከሰጡ መራጮችና ቁጥር አለመታረቅ፣
  4. የውጤት መግለጫ ቅጾችና የመራጮች መዝገብ ላይ ምርጫ አስፈጻሚዎች ፊርማቸውን በሠነዶቹ ላይ አለማሥፈራቸው፣
  5. ብዛት ያላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በአንድ ላይ ታጥፈው በድምፅ መስጫ ሣጥን ውስጥ ታጭቀው መገኘታቸው፣
  6. በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ለመስጠት ለተሠለፉ መራጮች ጊዜያዊ መታወቂያ ወረቀት በአካባቢ አሰተዳደር አካላት መታደል ናቸው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደ/ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (በኮንሶ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በዎላይታ፣ በጋሞ፣ በጌዴኦ፣ በጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአሌ፣ በአማሮ፣ በዲራሼ) ላይ ያካሄደው ሕዝበ ውሣኔ፤ ከዞኖቹና ከልዩ ወረዳዎቹ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች የደረሰውን ጊዜያዊ ውጤቶችን የማመሳከርና የማረጋገጥ ተግባራት ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል። በዚህም መሠረት የተረጋገጡ የ5 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች ውጤቶች በቦርዱ ፀድቀው ለሕዝብ ይፋ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የካቲት 13 ቀን 2015 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: