አቶ አማኑኤል ወጊሾ በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ከአንድ ወር በፊት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ውስጥ ‹‹ደቡብ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አዲስ ክልል ለመመሥረት ሕዝበ ውሳኔ ካደረጉ 11 አካባቢዎች መካከል፣ የዎላይታ ዞን በራሱ ክልል ሆኖ እንዲቋቋም ከሚደግፉና ከሚከራከሩ አካላት አንዱ ናቸው፡፡

በቅርቡ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ በተፈጠረ የሕግ ጥሰት በብሐራዊ ምርጫ ቦርድ ሙሉ ለሙሉ ስለተሰረዘው የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ፣ የዎላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ፣ የደቡብ ክልል የፖለቲካ ሁኔታ፣ እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችና የፓርቲያቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሪፓርተር ጋዜጣ ከአቶ አማኑኤል ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ ስለራስዎ ማንነት ይንገሩን?

አቶ አማኑኤል፡- እኔ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ነኝ፡፡ ፓርቲውን የተቀላቀሉኩት እንደምታውቀው አንድ ሰው ወደ ፓርቲ ለትግል ነው የሚገባው፡፡ መታገል ያለብህ ደግሞ አጀንዳዎች ሲኖሩህ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የነበሩ የረዥም ጊዜ ጭቆናዎች አሉ፡፡ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ እየተባባሱና እየተወሳሰቡ በመሄዳቸውና እኔም አንድ የማኅበረሰቡ አካል በመሆኔ ኑሮ ብዙም ሳይሻሻልላቸውና ሳይማሩ ያስተማሩን ወላጆቻችን እንደ አንድ ዜጋ ለማገልገል ቢያንስ ባለኝ ጊዜ የድርሻዬን መወጣት ይኖርብኛል፡፡ ለመታገል ደግሞ አመቺ የሚሆነው በተደራጀ መንገድ በመሆኑ፣ በተለይ ደግሞ ደቡብ አካባቢ ያለውን የፖለቲካ አሠላለፍ ሲታይ ጠንከር ብሎ ተደራጅቶ የሚታገል የፖለቲካ ኃይል ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው የደቡብ ክፍል ብዙም የጎላ ፖለቲካ ሲጫወት አይታም፡፡

በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት፣ በፖለቲካ ተሳትፎ ጭምር ገና በርካታና ብዙ ትግል የሚጠይቁ ጉዳዮች በመኖራቸው፣ በምችለው አቅም አንድ አሻራ ለማስቀመጥ አስቤ ነው ወደ ንቅናቄው የተቀላቀልኩት፡፡ በመሆኑም በተናጠል መታገል ጊዜና ጉልበት ከመጨረሱም በተጨማሪ፣ ትግሉን የሰመረ ሊያደርገው ስለማይችል ጠንካራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በአካባቢያችን የመገንባት ጉዳይ ዛሬ ነገ የሚባልለት ባለመሆኑ ፓርቲውን ልቀላቀል ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሙያዎት ምንድነው?

አቶ አማኑኤል፡- በሙያዬ መምህር ነኝ፡፡ በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የሒሳብ መምህር ነኝ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በአገር ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ እንቅስቃሴና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶችን በማየት ሁኔታዎችን እገመግማለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ዓላማ ይዘው ይመሠረታሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የእናንተ ፓርቲ የተመሠረተው በደቡብ ክልል በተለይም በወላይታ የደረሱ ጭቆናዎችንና በደሎችን ለመታገል የሚለው አንዱ ዓላማው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በወላይታ ላይ በተለየ ሁኔታ የደረሱ ጭቆናዎች አሉ? ፓርቲ ለመመሥረት ያበቃችሁ በወላይታ ላይ በተለየ ሁኔታ የሚነሳ ጉዳይ ካለ ቢጠቅሱልኝ?

አቶ አማኑኤል፡- አዎ በእርግጠኝነት የዎላይታ ትግል ወይም ደግሞ በዎላይታ ላይ የደረሰ ጭቆና አለ፡፡ እንደ ደቡብ ደግሞ ስታየው ይህ ደቡብ የሚባለው ክፍል በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም ሆነ በማኅበረሰባዊ ሁኔታዎች የተገለለ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ግን የማይተካ ሚና ሲጫወት የነበረ ነው፡፡ በሰላም ግንባታ፣ በፖለቲካዊም ሆነ በባህል ረገድ የደቡብ ክልል ራሱ በጥቅሉ ስንወስደው ያለ ምንም ማመንታት በሙሉ ልብ ለኢትዮጵያዊነት ራሱን የሚሰዋ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ዎላይታ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የራሱ መንግሥት ወይም ንጉሥ የነበረው፣ ከዚያ በፊት እስከ ሩቅ ምሥራቅ ድረስ የሚሠራ የራሱ መገበያያ ገንዘብ የነበረው ነው፡፡ ወላይታ በጣም ለም መሬት ነው፡፡ ለማዕከላዊ መንግሥት እስከ ቅርብ ድረስ ከዎላይታ በርካታ ምርት ይጫን ነበር፡፡ ሕዝቡ ታታሪ ነው፣ በዜግነቱም የሚታወቅ ነው፡፡ የመጨረሻው ንጉሥ ካዎ ጦና ሰባት ዓመት ሙሉ ከአፄ ምኒልክ ጋር ሲዋጋ የነበረ፣ በጣም የተደራጀ ጦርና ሰፊ የሆነ የራሱ ግዛት የነበረው ነው፡፡ ወላይትኛ ቋንቋ በአፍሪካ ጭምር ይታወቃል፡፡ ለአንድ ወላይታ በኢትዮጵያዊነትና በዎላይታነት መካከል ምንም ልዩነት የለውም፡፡ ዎላይታ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ተዟዙሮ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሥራ የሚሠራ ታታሪ ሕዝብ ነው፡፡ በማንነቱ የሚኮራ ገናና ሥርወ መንግሥት የነበረው፣ ቢሆንም በጊዜ ሒደት ውስጥ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ እያነሰ ሄዷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በመጡ ሥርዓቶች ከዚህ በፊት የነበረው የኢኮኖሚ አቅሙና የባህልና ታሪካዊ ሀብቶቹ ተዳክመዋል፡፡ አሁን በእኛ ዘመን በደርግም ሆነ በዚህኛው ሥርዓት ያለው ሁኔታ ሲታይ የኢኮኖሚ አቅሙ በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲያሽቆለቁል ያደረገው ምንድነው ?

አቶ አማኑኤል፡- እንደዚያ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት የሥርዓቱ ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት የለም፡፡ የሚመጣው መንግሥት በሕዝብ የምርጫ ይሁንታ ከሕዝብ ለሕዝብ የሚመጣ አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ የመንግሥት አመሠራረት በባህሪው ከደርግ በፊት የነበረው ዘውዳዊ አገዛዝ ነው፡፡ ሲሶ ለአራሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ፣ ሲሶ ለአንጋሽ እየተባለ አራሹ አንድ ሦስተኛውን ነበር የሚወስደው፡፡ ገበሬው ከመሬቱም ተገልሎ ያመረተውን ምርት አንድ ሦስተኛውን ብቻ ነበር ይዞ የሚገባው፡፡ ስለዚህ ያ የዘውዳዊ ሥርዓት በባህል፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ትልቅ ምስቅልቅል ነው የፈጠረው፡፡ ያን ተከትሎ የተማሪዎች ንቅናቄ እነ ኢብሳ ጉተማ፣ ዋለልኝ መኮንን፣ የወላይታ ወጣቶችም ጭምር እንደ ሰሎሞን ዋዳ የመሳሰሉት ዘውዳዊ ሥርዓቱን በመቃወም መሬት ለአራሹና የብሔር እኩልነት መስፈን አለበት ብለው በኢሕአፓም፣ በመኢሶንም ተደራጅተው ሲታገሉ የነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህ መሀል እነሱም በሚገባ ሳይደራጁ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት መጣ፡፡ ለውጥ ሲመጣ መሬት ለአራሹ የሚለው ጥያቄ መልስ አገኘ፡፡ ነገር ግን መሬት ለአራሹ መልስ ሲያገኝ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ እኩልነትና ሌሎች ጥያቄዎች ተዳፍነው ቆዩ፡፡ ሥርዓቱ በወታደራዊ አገዛዝ የሚመራ ስለነበር 17 ዓመት በሙሉ በጦርነት ነው ያሳለፈው፣ ልማት አልነበረም፡፡

መጀመርያ ከዘውዳዊ ሥርዓት የመጣ የተዳከመ ኢኮኖሚ ነበር፡፡ ወደ ሥልጣን የመጣው ደግሞ ወታደራዊ ሥርዓት ስለነበር ሕዝቡ ለውጥ ይፈልግ ነበር፡፡ በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎች የወለዱት የንቅናቄ ለውጥ በወታደራዊ መንግሥት ተቀለበሰ፡፡ ያ ወታደራዊ መንግሥት ደግሞ 17 ዓመት ሙሉ በጦርነት አሳለፈ፡፡ ከዚያ ሕዝቡ ልጆቹን ለጦርነት መገበር ጀመረ፡፡ ያ ጦርነት አለፈ፣ የኢሕአዴግ ሥርዓት መጣ፡፡ ነገር ግን ይህ ሥርዓት ሲመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውንና ያልተፈታውን ጥያቄ እፈታለሁ ብሎ ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ በሕገ መንግሥት ደረጃ አስቀመጠው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ብሔር ብሐረሰቦች በሕገ መንግሥት የተሰጣቸውን የዴሞክራሲ መብትና በአካባቢያቸው ጉዳይ የመወሰን ሥልጣን ሳይሰጣቸው በከፊል በሕገ መንግሥት ደረጃ ለመመለስ ሞከረ፡፡ በተወሰነ ደረጃ በቋንቋቸው ትምህርት እንዲያገኙ አደረገ፣ የተወሰነ ባህል ላይ ዕውቅና ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የመወሰን ሥልጣን አሁንም በማዕከላዊ መንግሥት ነው የተያዘው፡፡

ስለዚህ የልማት ጉዳይ፣ በራሱ ጉዳይ ራሱ ወስኖ የመሥራት ሥልጣን ሕዝቡ አላገኘም፡፡ የሚፈለገውን ልማት ማምጣት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ይኼኛው ሥርዓት እየቆየ ጭራሹን አምባገነን እየሆነ መጣ፡፡ በተለይ ደግሞ በደቡብ ክልል ሥርዓት አልበኝነትና ሙስና ተበራከተ፡፡ እርስ በርስ ተናቦ የመወሰን ሥልጣን አልነበረም፡፡ ሁሉም የሚሠራው በኔትወርክ ተሳስሮ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የዎላይታ ወጣት በሒደት እየፈለሰ ከአካባቢው ወጣ፡፡ አሁን ካየህ የወላይታ ወጣት የሌለበት ቦታ የለም፡፡ በተለይ ባለፉት ስምንትና አሥር ዓመታት ውስጥ ወጣቱ ወደ ከተማ እየፈለሰ ወጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የዎላይታን ወጣት ምንድነው እንዲፈልስ ያደረገው?

አቶ አማኑኤል፡- የሥራ ዕድል ችግር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አርሶ አደሩ አምርቶ ልጆቹን መመገብ አልቻለም፡፡ በደቡብ ክልል ውስጥ ሁሉም ብሔረሰቦች በአንድ ላይ በነበሩበት ጊዜ አንዱና ትልቁ ችግር ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የለም፡፡ ሁለተኛ መሠረተ ልማት አልተዘረጋም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ለአርሶ አደሩ የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓቶች በተገቢው መንገድ አይቀርቡም፡፡ ይህ የሆነው የበጀት ክፍፍሉ በሕዝቡ ቁጥር ልክ ባለመከፋፈሉ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ጋ ያለው ጭቆና ድርብርብ ነው፡፡ ሕዝቡ ምንም እንኳ ለም መሬትና ጠንካራ የሥራ ባህል ቢኖረውም መቋቋም ባለመቻሉ ያለው አማራጭ መሰደድ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከዚህ በፊት ወጣት የሚባለው ክፍል ነበር የሚሰደደው፡፡ አሁን ግን ገበሬውም ሕፃናቱን ወደ ትምህርት ቤት መላክ አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳ የወላይታ የትምህርት ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ሕፃናቱም ከቀዬአቸው ለቀው እየወጡ ነው፡፡ በሕገወጥ የሕፃናት ዝውውር የደቡብ ክልል አንደኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የዎላይታ ወጣት በተለያዩ አካባቢዎች ለሥራና ለተሻለ አማራጭ ተሰዷል ብለዋል፡፡ ይህ ከፍተኛ ችግር መሆኑን የሚያሳይ ጥናት አድርጋችሁ ታውቃላችሁ? ምን ያህል ወጣቶች እንደፈለሱ መረጃ አላችሁ?

አቶ አማኑኤል፡- የተጠናቀረ የጥናት መረጃ የለም፡፡ ነገር ግን እኔ የሚሰማኝ የተማረ ሰው ሊሠራ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ይንቀሳቀሳል ይህ ጤነኛ ነው፡፡ ይህንን ፍልሰትም አትለውም፣ የሥራው ባህሪው ነው፡፡ እኔ ግን እያልኩህ ያለው ፍልሰት ዜጋው ባለበት አካባቢ እንዲቆይ የሚያደርግ የኢኮኖሚ አቅም መፈጠር ሳይችል ሲቀር የሚፈጠረውን ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ወጣቱ ከቀዬውና ከመኖርያው እየተፈናቀለ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ይሰደዳል፡፡ አሁን እዚያ አካባቢ ባለው የሕገወጥ የሕፃናት ዝውውር ኔትወርክ ውስጥ የፖሊስና የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ በርካታ ኃይሎች ይሳተፉበታል፡፡ በዚህ የተነሳ እኛ ወላይታን ባለቤት አልባ የሆነ ሕዝብ ብለን እንጠራዋለን፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰው ሲሰደድ ወላይታ ውስጥ ያለው የተሰደደውን የት ሄደ አይልም፣ ተሰዶ የወጣውም በየሄደበት ማንም አያውቀውም፣ ያልተመዘገበ ነው፡፡ ስለዚህ ተንቀሳቃሽ ሆኖ እዚያም እዚህም ሳይታወቅና ሳይመዘገብ ባለቤት አልባ ይሆናል፡፡

የሚገርምህ የዎላይታ ሕዝብ ቀና ነው፡፡ ደቡብ ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር መጀመርያ ትምህርት ቤት የተከፈተው ዎላይታ ውስጥ ነው፡፡ ከዘመናዊ ትምህርት ውጪም በወንጌላዊ ትምህርት የሚታወቁ የፕሮቴስታንት መምህራን የዎላይታ ልጆች ናቸው፡፡ እናም የዘመናዊ ትምህርት ፋና ወጊ የነበረ፣ የሥልጣኔ መነሻ የነበረ ሕዝብ አሁን ልጆቹ ተሰደው ከቀዬው ከወጣ አካባቢው ባዶ ነው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አሁን በአራት ክልሎች ሊደራጅ ተቃርቧል፡፡ የደቡብ ክልል ሕዝብን እየተዘዋወርን ስንጠይቅ ሁሉም በደል ደርሶብናል፣ ኢፍትሐዊነት ሰፍኗል የሚል ጥያቄ ነው የሚነሳው፡፡ በዚህ ሒደት ሁሉም ብሔር ክልል ለመሆን ከጠየቀና በደል የሚያነሳ ከሆነ ማን በዳይ ማን ተበዳይ መሆኑ ነው?

አቶ አማኑኤል፡- ከመጀመርያው ሕገ መንግሥቱ ከመረቀቁ በፊት ይህ ክልል አምስት ክልሎች የነበሩበት ነበር፡፡ ከዚያ ሁሉንም ጠቅልለው አንድ አደረጉት፡፡ በዚህ የተነሳ ምን ተፈጠረ? ማዕከላዊ መንግሥት የሚሾማቸው ለሥርዓቱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ነው፡፡ የአምባገነን ሥርዓት የመጀመርያ ባህሪው አመራር በሕዝብ የሚወደድ ከሆነ ሥልጣን ላይ አይቆይም፡፡ ይህ የአምባገነን ሥርዓት ነባራዊ መለያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ባህል ሆኗል፡፡ በዚህም የተነሳ የደቡብ ክልል ሲመሠረት በክልሉ የተዋቀረው የፖለቲካ ዘዋሪ ለሕዝብ የሚቆረቆር፣ ሥርዓት ያለው፣ የሕዝብ ውክልና ተሰጥቶት የተመረጠና የተሻለ አፈጻጸም ያለው ኃይል አይደለም፡፡ ይህ ኃይል የመጣው በኔትወርክ ትስስር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ በኔትወርክ የመጣ ኃይል ተጠሪነቱ ለሕዝብ ሳይሆን ላመጣው አካል ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው ኔትወርክ ከፌዴራል መንግሥት ጋርም ተመሳሳይ ኔትወርክ አለው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚሆነው ምንድነው? ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ጠንካራ ኔትወርክ ያለው ክልሉን እንደፈለገ ማሽከርከር ይችላል ማለት ነው፡፡ እነዚህ አካላት የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሁን አይሁን የመጣውን አቅጣጫ ማስፈጸም ነው ተግባራቸው፡፡ ክልሉ ውስጥም ተመሳሳይ የሆነ የኔትወርክ ሹመት ነው ያለው፡፡ በዚህ የተነሳ የትኛውንም ብሔረሰብ ብትጠይቅ ተጠቅሜያለሁ የሚል የለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ስታይ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ብሔረሰብ ተጠቅሜያለሁ የሚል የለም፡፡ የሚጠቀሙት የተደራጁ የፖለቲካ ልሂቃን ከባለሀብቱ ጋር በመሆን ነው፡፡ ስለዚህ እየተፈጠረ ያለው ጥቂት የሆኑ ካፒታሊስቶች የሚዘውሩት ሥርዓት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ዎላይታ ራሱን ችሎ ክልል ሆኖ ቢቋቋም ችግሩን ሊፈታው ይችላል?

አቶ አማኑኤል፡- በዓለም ላይ አብሮ መሆን ይመረጣል፡፡ ዓለም ወደ አንድ ትብብር እየመጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ወደ አንድ መምጣቱ ይመረጣል፡፡ ነገር ግን ይህ አንድነት ለአንተ የተሻለ ለውጥ የሚያመጣው ጥቅምህን የሚያስጠብቅልህ ሲሆን ነው፡፡ ነገር ግን በአንድነት ውስጥ አንተ ምንም የማትጠቀም ከሆነ ለምሳሌ እንግሊዝን ማየት ትችላለህ፡፡ መጀመርያ የአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ነበረች፡፡ ነገር ግን የእንግሊዝ ሕዝብ ከአውሮፓ ኅብረት የወጣበት ምክንያት መቼም አብዶ አይደለም፡፡

ነገር ግን አገሩን እዚያ ኅብረት ውስጥ ትናንትን አይቷል፣ ዛሬ ግን በዚህ ኅብረት ተጠቃሚ ባለመሆኑ ነው ለቆ የወጣው፡፡ ስለዚህ ወላይታን ስናይ አንደኛ የተሻለና የተማረ ሕዝብ ያለው ነው፡፡ ወላይታ ለራሱ አይደለም በአገር ደረጃ በፌዴራል መዋቅር ውስጥ ወላይታዎች አገልግለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ነገር ግን እነሱ የወጡበትና ተወክሏል የተባለውን የኅብረተሰብ ክፍል ግን በተወከሉበት ልክ ሊያገለግሉት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ሥርዓቱ በሕዝብ ውክልናና ተጠያቂነት መጠን እንዲያገለግሉ አላደረገም፡፡ እንዲያው ሥርዓቱን እንዲያገለግሉ በመሆኑ በአጠቃላይ የሥርዓት አገልጋይ ናቸው፡፡ ስለዚህ አማራም፣ ኦሮሚያም፣ ደቡብም ሆነ ሌላው ጋ ብትሄድ የሕዝቡ ሕይወት ከቀን ወደ ቀን ችግር ውስጥ እየባ ነው፡፡ ሀብቱ የሚሄደው ጥቂቶች ዘንድ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ብዙ የወላይታ ሰዎች የሥልጣን ባለቤት ነበሩ፡፡ ይህን ስታይ ወላይታ እንደጨቆነ አድርገው የሚናገሩ አሉ፣ የሚገርምህ በተለያዩ ጊዜያት ይህንን እንሰማለን፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ የወላይታ ሕዝብ የወላይታ ዞን ክልል ሆኖ እንዲቋቋም የሚያቀርበው ጥያቄ ቢሳካ ምን የተለየ ጥቅም ያገኛል?

አቶ አማኑኤል፡- ለምሳሌ ዎላይታ ውስጥ አንድ የኢንዱስትሪ ፓርክ የለም፡፡ በዓመት ቢያንስ እስከ 100 ሺሕ ወጣት ሥራ አጥ ይሆናል፡፡ ተመርቆ ሦስት ዓመት አራት ዓመት ሥራ አጥ ይሆናል፡፡ በርካታ ልጆች ዲግሪ ይዘው ወደ መከላከያ ይገባሉ፣ መከላከያ መግባት ነውር ባይሆንም፡፡ አንድ እናት ልጇን አስተምራ ሲመረቅላት የተሻለ ሥራ አግኝቶ እንዲጦራት ነው የምትፈልገው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ለዚህ ታታሪና ሥራ ለማይንቀውና ተግባቢ የሆነ የወላይታ ሕዝብ ይህን ያህል የሥራ አጥ ቁጥር ይዞ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማምጣት አንድ ኢንዱስትሪ እንኳ ቢገነባ ችግሩን ሊያስታግስ ይችላል፡፡ ሌላው አስቸጋሪ ነገር የወላይታ ሕዝብ በተሰደደ ቁጥር ከባህሉ እየራቀ ባህሉን እየረሳ ከሆነ፣ ከጊዜ በኋላ ሠፈሩን ሳይቀር ሊረሳ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከቤቱ የሚወጣው ወጣት ገና በአሥርና በ12 ዓመቱ ነው፡፡ ይህ ልጅ ከአካባቢው ሲወጣ ባህሉንና ማንነቱን ይረሳል፡፡ ታሪኩንም፣ ቋንቋውንም ይረሳል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የሚሰደደው እየበዛ በሄደ ቁጥር የባህልና የማንነት መክሰም ይፈጠራል፡፡ ሕዝቡ የማንነት አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡

ስለዚህ ወላይታ በቂ የሆነ የተማረና ታታሪ ሕዝብ አለው፡፡ በተለይም በአንድ አገር ኢኮኖሚ የሚፈለገው የተማረና ታታሪ ሕዝብ በመሆኑ ለምሳሌ እንደ ቻይና፣ ኮሪያ ጃፓንና መሰል የእስያ አገሮች ያደጉት በታታሪና በተማረ ሕዝብ ነው፡፡ እኛ በደቡብ ክልል ውስጥ ተካተን በመኖራችን ያየነውና የተደረገው ነገር ውጤታማ ያልሆነ፣ በሙስናና በኔትወርክ የተጠላለፈ ነው፡፡ ካድሬው ተጠሪነቱ ለሕዝብ ሳይሆን ለማዕከላዊ መንግሥት በመሆኑ፣ ለሕዝቡ ልማት ሊያመጡ የሚችሉ ኃይሎች የተሰባሰቡበት አይደለም፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ እንዲያው ዝም ብሎ ደቡብ የኢትዮጵያ የብዝኃነት ማሳያ ተባለ እንጂ፣ እንደ ተምሳሌት በፌዴራል ሥርዓቱ ይመራ እንጂ፣ ውስጥ ያሉት ብሔሮች እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው በተፈጥሮ የነበራቸው ትስስር ነው እንጂ፣ በፌዴራል ሥርዓቱ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ወላይታነት ወይም ሲዳማነት በኢሕአዴግ አይደለም የተፈጠረው፡፡ አንድ ላይ በመሆናቸው ብቻ የኅብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት ተብለው የሙዚቃ ማጀቢያ ነው የሆኑት፡፡ ነገር ግን ይህንን ስብስብ በጥሩ ፖለቲካ ሕዝቡን ተጠቃሚ በማድረግ ይህን ብዝኃነት ማግነንና ማድመቅ ይችሉ ነበር፡፡ ሹመቱ በ56 ብሔሮች የጋራ ዓላማ በያዙና የሕዝብ ውክልና ይዘው በመጡ ቢሆን፣ ከእነሱ አልፈው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የኃይል ሚዛን ማስጠበቅ ይችሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየተፈጠረ ላለው የእርስ በርስ ሽኩቻና በሚጣሉ ኃይሎች መካከል ለተፈጠረው ውዝግብ መባባስ ምክንያት የእነዚህ የ56 ብሔረሰቦች ዝምታ ነው፡፡

ምክንያቱም እነዚህ ሕዝቦች እንደ አንድ ኃይል ሆነው የፖለቲካ ሚዛኑን ማስጠበቅ ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ክልል የወጡ የፖለቲካ ልሂቃን የአሸናፊ ተለጣፊ ሆነዋል፡፡ ተላላኪ ናቸው፡፡ መቼም ተላላኪ አድርግ የተባለውን እንጂ የራሱ ዕቅድ የለውም፡፡ ስለዚህ ይህ ክልል ተላላኪ ከሆነና የራሱ ዕቅድ ከሌለው እንዴት ብሎ ልማትና ዴሞክራሲ ያመጣል?

ሪፖርተር፡- አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከዚህ ክልል ወጥተው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው ለክልሉና ለወላይታ ምን አበረከተላችሁ?

አቶ አማኑኤል፡- የአቶ ኃይለ ማርያም ወደ ሥልጣን መምጣት ሲታይ፣ በእኛ አገር ፖለቲካ የሆነ አካል ከአንተ አካባቢ መጥቶ ሥልጣን ሲይዝ ሕዝቡን አይወክልም፡፡ ምክንያቱም በሕዝቡ ስም ይወከልና ሕዝቡ እከሌ አለ፣ ተክሎልኛል ይልና እንዲታለል የሚደረግበት አሠራር ነው፡፡ ይህ የአፍሪካ አምባገነኖች አሠራር ነው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም አንድ ግለሰብ ናቸው፡፡ በእርግጠኝነት ለመናገር የምችለው እሳቸው እዚያ ቦታ ላይ በመሆናቸው የተለየ ነገር ለወላይታ ወይም ለደቡብ ክልል ፈጥረዋል ለማለት አልችልም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ እሳቸው የዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል የእምነት ተቋም ውስጥ ያደጉ ለዘብተኛ ናቸው፡፡

ስለዚህ እሳቸው ወደፊት ተስፋ የሚያደርጉት የሚያልሙት ፍትሕን ለማምጣት፣ እኩልነትን ለመፍጠር ይመስላል፡፡ ነገር ግን እሳቸውን ከቦ ያለው ቡድን የሚያስበውን የሚያስቡ፣ እሳቸው አንድ ግለሰብ በመሆናቸው ፖለቲካ በጋራ ውሳኔና በአጀብ የሚተገበር ሥራ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ብቻቸውን ከመጡበት የአካዳሚክስና የእምነት ተፅዕኖ፣ እንዲሁም በእሳቸው ዙሪያ ባሉ ሰዎች ጫና የተነሳ የተለየ ነገር ማድረግ አይችሉም፡፡ እሳቸውም የተለየ ነገር የማድረግ ዕሳቤውም አይኖራቸውም፡፡ ነገር ግን እሳቸው በመቀመጣቸው ለእኛ ነው ጦሱ የተረፈው፣ ምክንያቱም አቶ ኃይለ ማርያም እዚያ ቦታ በመቀመጣቸው ሌሎቹ የሚያስቡት ወላይታ እየተጠቀመ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚመነጨው ከኖርንበት የፖለቲካ ባህል ማለትም አንድ ባለሥልጣን የሆነ ቦታ ላይ ሲቀመጥ ጥቅም አለው ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ነገር ግን እሳቸው እዚያ ቦታ በመቀመጣቸው ለኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ የሚጠበቅባቸው ሚና ተጫውተዋል አንልም፡፡ የተለየ ነገር ማድረግ ቀርቶ የምንመኘውን ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ቢቻል መልካም ነበር፣ ምንም እንኳ ሥርዓቱ ይህን ለማድረግ ሊፈቅድላቸው ባይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ አዲስ ክልል ለመመሥረት በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ በወላይታ ዞን በተፈጠረ የሕግ ጥሰት፣ የዞኑ አጠቃላይ ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ከምዝገባው ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተሰርዟል፡፡ ይህን ውሳኔ እንዴት አገኙት?

አቶ አማኑኤል፡- እኛ እንግዲህ እንደ ዎላይታ በርካታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች አሉብን፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ሊነሱ የቻሉት የሕዝቡ የመወሰን ሥልጣን በማጣቱ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ያለን አማራጭ በጋራ ሆነን መጠቀም ካልቻልን ልክ እንደ እንግሊዝ አብረን ሆነን ዓይተናል፡፡ ከዚያ ያለውን እንቅስቃሴ ገመገምን፣ ሌሎች ክልሎች ለምሳሌ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ ወይም ሌሎችንም ስታይ የክልሉ ምክር ቤት ሙሉ ወይም በአብዛኛው የአንድ ብሔር ውክልና ነው ያለው፡፡ ይህ ማለት የአብላጫው ዴሞክራሲ በአንድ ዓይነት ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ ይተገበራል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በደቡብ ክልል ውስጥ የነበረው ከ56ቱም ብሔር ብሔረሰቦች ተሰባስበው በእያንዳንዱ ጉዳይ ይወስናሉ፡፡ በዚህ ውስጥ ኔትወርክ ይዘረጋል፡፡ ከኔትወርኩ ከወጣህ ትመታለህ ማለት ነው፡፡ ይህንንም ገምግመን ካየን በኋላ የሕዝቡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህልና ሌሎች ጉዳዮች ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ያለን አማራጭ ወደ አንድ ቦታ መምጣት አለብን በሚል ሕዝቡ በራሱ ክልል ሆኖ መደራጀት ፈለገ፡፡ ይህ ጥያቄ የቆየ ነው፡፡ ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ የኖረ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ተገድለዋል፡፡ ባነሱት የክልልነት ጥያቄ ምክንያት በዎላይታ አሁን የምታየው የተሻለ የልማት እንቅስቃሴ የመጣው ዞን ሆኖ ከተቋቋመ ወዲህ ነው፡፡ በሌላ በኩል በዎላይታ የምታያቸው በርካታ ልማቶች በወላይታ ልማት ማኅበር የተሠሩ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ራሳችንን ሆነን እንደራጅ የሚባለው ጉዳይ በሕዝቡ ሲጠየቅ፣ በክላስተር ተደራጅተህ ሌላ መዋቅር ውስጥ ግባ ሲባል ሕዝቡም አልፈልገም አለ፡፡ እዚያ አካባቢ ያለውን ካድሬም ክላስተር ምንድነው ብለህ ብትጠይቅ ምኑንም አያውቁትም፡፡ አንዳንዶቹ እንዲያውም ዓብይ (ዶ/ር) ብቻ ነው የሚያውቀው ይላሉ፡፡

ስለዚህ እነዚህ ካድሬዎች በማያውቁት፣ እኛ እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ ባልተወያየንበትና በማናውቀው፣ ሕዝቡም ባልገባው የአደረጃጀት ሥርዓት በክላስተር ተደራጅ ተብሎ ተፈረደበት፡፡ በመጀመሪያ የተደረገው አስገራሚ ነገር የወላይታ ሕዝብ በክልል ለመደራጀት ያነሳው ጥያቄ ሲበረታ፣ ይህንን ጥያቄ ለመቀልበስ በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ሁሉም ብሔረሰቦች የክልልነት ጥያቄ በተናጠል እንዲያያቀርቡ ተደረገ፡፡ ይህን በግምገማቸው ላይ የወጣ መረጃ ነው፡፡ ይህን ካደረጉ በኋላ ሁሉም ብሔረሰብ ጥያቄ ሲያነሳ ለዚህ ሁሉ እንዴት ብለን የክልልነት ጥያቄ እንፈቅዳለን? ለ56 ብሔረሰብ ክልል መስጠት አይቻልም የሚል ሴራ ተጠነሰሰና የወላይታን ጥያቄ አፍነው ያዙት፡፡ በዚህ የተነሳ ይህ ኃይል በራሳችን የመብት ጉዳይ ገብቶ ሲፈተፍት ሕዝቡ ዋጋ እንዲከፍል ተደረገ፡፡ በመጨረሻ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጉዳዩ ተልኮ በክላስተር ይደራጁ በሚል 11 መዋቅሮችን ወደ አንድ አምጥተው ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ተወሰነ፡፡

ይህ የክላስተር አወቃቀር የሚኖረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ምንድነው የሚለው በተገቢው ሁኔታ ጥናት አልተደረገበትም፡፡ ቀጥታ ከማዕከል መጣ ተብሎ ወደ ሥራ ተገባ፣ ነገር ግን የሕዝቡ ፍላጎት አልነበረም፡፡ ካድሬው ያልሞከረው ነገር የለም፣ ሕዝቡ ግን በአቋሙ እንደፀና ነው፣ ክላስተሩን አልደገፈም፡፡ ከደገፉት ካድሬዎች ውስጥም እንዲያው አውጥተው በአፋቸው አይናገሩ እንጂ አብዛኞቹ አይደግፉትም፡፡ እንዲያውም ወላይታ ክልል እንዲሆን ነው የሚፈለገው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በተከታታይ አቤቱታና ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ በመጨረሻ የብልፅግና አቅጣጫ ነው ተብሎ ሲቀርብ፣ እኛ ግን ያቀረብነው ሐሳብ ወላይታ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ፣ እንዲሁም በክላስተር እንዲደራጅና ከነባሩ ክልል ጋር እንቆይ የሚል ሦስት ዓይነት አማራጭ ለሕዝቡ ይቅረብለት የሚል ነው፡፡ ግን የሚሰማን አላገኘንም፡፡

በዚህም ወደ ሰላማዊ ሠልፍና መሰል አንጃ ግራንጃ ከገባን አሁን ያለው የፖለቲካ አየር ጥሩ ባለመሆኑ፣ ሕዝቡ ከዚህ በፊት ያለግባብ በርካቶች እንደተገደሉበትና እንደተወሰዱበት ዕርምጃዎች ዓይነት ችግር ውስጥ ማስገባት ስለሌለብን፣ ያለን አማራጭ ሰላማዊ ትግል ነው በሚል የሕዝብ ውሳኔውን ላለመሳተፍ ወሰንን፡፡ በመጨረሻ ሕዝቡ በሕዝበ ውሳኔው አልሳተፍም ሲል ካድሬው ካርዱን በፊርማ አውጥቶ በጣት አሻራ፣ በጣት አሻራ አውጥቶ በፊርማ ኮረጆ ውስጥ አስገባው፣ አንዳንድ ቦታ ላይ ደግሞ 40 እና 50 ካርድ ጠቅልሎ አስገባ፡፡ ይህ እንግዲህ ታሪካዊ ቅሌት ነው፡፡ የፖለቲካ ውድቀትም ነው፡፡ ዋናው ስኬት የሕዝቡ የትግል ውጤት መታየቱ ነው፣ የሕዝቡ የአቋም መፅናት ውጤት ነው፡፡ ከዚህ በፊት የደረሰበት የኢኮኖሚ የፖለቲካና የመልካም አስተዳደር ችግር ውጤት ነው፡፡ በመጨረሻ እንዳየኸው ቦርዱ በአጠቃላይ የወላይታን ሕዝበ ውሳኔ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ሪፖርተር፡- ለቀጣይ የታቀደው ምንድነው?

አቶ አማኑኤል፡- አንደኛው ሕጋዊ መንገድ ነው፡፡ ይህም ማለት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔው እንደገና እንዲታይ እንጠይቃለን፡፡ አሁን ከሕግ ባለሙያዎች ጋር እየመከርን ማቅረብ ያለብንን ጉዳይ ለመጠየቅና ተጨባጭ ሁኔታዎች ለማሳየት እየሠራን ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ፈታኝ ነው፣ ነገር ግን ሕዝቡን አነቃቅቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- የብልፅግናን ጉዞ እንደ ፓርቲ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?

አቶ አማኑኤል፡- እንግዲህ ገዥው ፓርቲ እርስ በርሱ አንድ ላይ ቆሞ መዘመር አልቻለም፡፡ እንደ ፓርቲም አይደሉም፡፡ እንኳን ገዥ ፓርቲ ተፎካካሪ ፓርቲ እንኳ አመራሩ ተመካክሮ አንድ ላይ መቆም ካልቻለ ፓርቲ የለም አይደለም አገር የራሱን አባላት ማንቀሳቀስ አይችልም፡፡ አንድ ውሳኔ ለመወሰን ሁለት ወይም ሦስት ወራት ሊወስድበት ይችላል፡፡ ምናልባት የኃይል ዕርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን በጋራ መግባባት ውሳኔ መስጠት አይችልም፡፡ በጋራ መግባባት ያልወሰንከው ውሳኔ ውጤቱም ያው ነው፡፡ ስለዚህ ዓይተህ ከሆነ የፓርቲው አባላት እርስ በርሳቸው ይጠዛጠዛሉ፡፡ በተለይ የአማራ ብልፅግናና የኦሮሚያ ብልፅግና አካሄድን ዓይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ ይህ ችግር መፈታት አለበት፡፡ ምክንያቱም አንደኛ አገሪቱን አላስፈላጊ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተታት ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ለዘብተኛው፣ አደገኛውና ፀረ ዴሞክራሲ የሚሆነው በተለይ የደቡብ ክልልም ሆነ ሌላው ኃይል የቀውስ ዋና ማዳበሪያ ሆኖ እያገለገለ ድምፁን አጥፍቶ እየኖረ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት እኮ የባለቤትነት ስሜት ማጣት ነው፡፡ የሚመጣው ችግር በጋራ ነው የሚበላን፡፡ ችግር ሲፈጠር እያየህ ዝም ማለት የችግሩ ተባባሪና ዋነኛ ተዋናይ ነህ ማለት ነው፡፡ በነገርህ ላይ ሁለት ኃይሎች በተለያየ ሐሳብ ይጣላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አስታራቂ እንኳን የለም ይባላል፡፡ ቢያንስ አንተም ተው አንተም ተው የሚል ከሌለ መዘዙ ከባድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የፓርቲ ሥርዓቱን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከቶታል፡፡ ለውጥ መጣ ሲባል አምባገነን ሥርዓትን በጋራ ለመለወጥ እንጂ፣ ሥርዓቱን ከጣሉ በኋላ ሊከናወኑ ስለታሰቡ ጉዳዮችና ሊገነቡት ያሰቧት ኢትዮጵያ ላይ የዕይታ ልዩነት አለ፡፡ ምክንያቱም ምን ዓይነት ዴሞክራሲ ነው የምንገነባው? ምን ዓይነት ኢትዮጵያ እንፍጠር? በሚለው ጉዳይ ለውጥ ያመጣው ኃይል የጋራ ዕይታ፣ ስምምነትና ዕቅድ የለውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ተግባር በርካታ አገሮች ታይቷል፡፡ ብዙ ጊዜ በሰላማዊ ትግል የሚመጡ ለውጦች መንገድ ላይ የሚቀሩት አምባገነን ሥርዓትን ማፍረስ ላይ ይስማማሉ፡፡ ነገርን ምን ዓይነት ዴሞክራሲ እንገንባ የሚለው ላይ ስምምነት ስለማይኖራቸውና ዕቅድ ስለማይነድፉ ሒደቱ ይከሽፍባቸዋል፡፡

እንዲያውም አንዳንዴ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፎ የወታደራዊ መንግሥት አገዛዝ የሚመጣበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ያልተጠበቀና ከመጀመሪያው የባሰ ችግር ያመጣል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የብልፅግና ሰዎች ያለውን ሥርዓት ማስወገድ ላይ እንጂ ምን እንሥራ የሚል መስመር አልነበራቸውም፡፡ ደጋፊዎቹን እንኳን ስታይ ትናንት መልዓክ መጣ ሲሉ የነበሩት የጨፈነውን ዓይናችንን ስንከፍት ይህ አውሬ ሥርዓት፣ ሰው በላ ሥርዓት መጥፋት አለበት ብሎ ሌላ ጥግ ላይ ቆመዋል፡፡ የነበረው ድጋፍ ያኛውን ሥርዓት የመለወጥ እንጂ በአዲሱ መንገድ ላይ አቋም የለውም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ደጋፊውም ገብቶት ሳይሆን በጥላቻና በሐሰት ትርክት ላይ ተመርኩዞ ነበር ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲያችሁ የወላይታ ንቅናቄ ምን ዓላማና ርዕዮተ ዓለም ይዞ ነው የተመሠረተው?

አቶ አማኑኤል፡- ፓርቲያችን የሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ይከተላል፡፡ ለዚህም ዋና ዋና ምክንያቶቹ የመጀመሪያው ነፃነት፣ ሁለተኛው እኩልነት፣ ሦስተኛው አጋርነት ወይም ወንድማማችነት ናቸው፡፡ ነፃነት ከሊበራል ነፃነት ይለያል፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ መሠረታዊ ነፃነትን ነው እንደ ነፃነት የሚከተለው፡፡ የሶሻል ዴሞክራሲ ነፃነት ግን የመናገር፣ የመጻፍ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ከሚለው ወጣ ብሎ አንድ ሰው ትምህርት ቤት መሄድ ካልቻለ ነፃ ትምህርት ተብሎ በሕግ መቀመጡ ምን ያደርግለታል፡፡ ስለዚህ ነፃነት ሁለት ጉዳዮች አሉት፡፡ እነዚህ የማኅበራዊና የፋይናንስ ነፃነቶች መኖር አለባቸው፡፡ ማኅበረሰቡን የመማርና የመናገር ነፃነት ብቻ ብለህ ሳይሆን እንዲማር አስቻይ ሥርዓት መፍጠር አለብህ፡፡ በኢኮኖሚውም የገበያ ነፃነት ብለህ ብቻውን ብታስቀምጥ ምንም ዋጋ የለውም፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መኖር አለበት፡፡ ምክንያቱም በማኅበረሰቡ ውስጥ በተለያዩ አጋጣሚ የተጎዳ ወይም ተጎጂ የኅብረተሰብ ክፍል አለ፡፡ የአካል ጉዳተኞችና የሴቶች ተጠቃሚነት፣ የገጠርና የከተማ ልዩነቶች በመንግሥት ድጋፍ መታገዝ አለበት፡፡ የባህልም ልዩነት አለ፣ ይህንንም አካታች በሆነ ሥርዓት መደገፍ አለብህ፡፡ ለሁሉም እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ካልፈጠርክ ሕገ መንግሥት ውስጥ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው በሚል ብቻ አስቀምጠህ እኩልነቱን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ካልቻልክ የትም አትደርስም፡፡ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች በብሔርና በማንነት የተከፋፈለ ማኅበረሰብ ውስጥ የተሻለ አማራጭ ለማቅረብ የሶሻል ዴሞክራሲ ተመራጭ ነው፡፡ የሆነ የሕግ ሥርዓትና ክትልል በሌለበት ገበያው በራሱ ይዳኝ ብለህ ብትለቀው አሁን እንደሚታየው የተወሰኑ ሀብታሞች ይቆጣጠሩታል፡፡ መንግሥትም መስመሩን ይስታል፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣይ ዕቅዶቻችሁ ምንድናቸው?

አቶ አማኑኤል፡- የሕዝባችን የፍትሐዊነትን ጥያቄ እስኪመለስ ሰላማዊ ትግል አጠናክሮ መቀጠልና በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ ያልተለመደውን የተተኪ አመራር ማፍራት ላይ እንሠራለን፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ችግር ተተኪ አመራር ባለመኖሩ ነው፡፡ ብዙ ችግር እየተከሰተ ያለውም ተተኪ ከሌለ ፖለቲካው የጥቂቶች ይሆንና አብዛኛው ተላላኪ ብቻ ሆኖ የሚቀረው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት 53 ፓርቲዎች በአንድ ላይ ለምርጫ መቅረብ ለገዥው ፓርቲ ድጋፍ ከመሆን ውጪ ዴሞክራሲው የይስሙላ ስለሚሆን፣ ይህ አካሄድ መቆም አለበት፡፡ በተለይ አሁን የጀመርነው ነገር አለ፡፡ በደቡብ ያለውን የፖለቲካ ኃይል ወደ አንድ ማሰባሰብና ወደ ግንባር ማምጣት፣ ከዚያም ከሌሎችም ጋር በተለይ በርዕዮተ ዓለም በምንስማማቸው ጉዳዮች አብረን እንሠራለን፡፡ በጋራ አጀንዳ በጋራ ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ ሌላው በአካባቢያችንና በኢትዮጵያ የተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ መሥራትና ገዥው ፓርቲ የማያያቸውን መንገዶች ማየትና ማሳየት የሚሉትን በጥቂቱ መውሰድ ትችላለህ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: