

በደቡብ ክልል ጫሞ ሐይቅ ላይ በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ ስምንት ሰዎች፤ ባጋጠማቸው የማዕበል አደጋ ምክንያት ሰጥመው ህይወታቸው ማለፉን የአማሮ ልዩ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በአደጋው ከሞቱት ውስጥ እስካሁን የሁለት ሰዎች አስክሬን በፍለጋ መገኘቱንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
የአማሮ ልዩ ወረዳ አልፋጮ ቀበሌ ነዋሪዎችን አሳፍሮ ወደ አርባ ምንጭ በመጓዝ ላይ በነበረው ጀልባ ላይ የመገልበጥ አደጋ የተከሰተው፤ ትላንት ቅዳሜ መጋቢት 16፤ 2015 ከሰዓት በኋላ መሆኑን የልዩ ወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አራጋው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በጫሞ ሐይቅ ላይ በነበረው ማዕበል፤ የጀልባውን ሹፌር ጨምሮ ስምንት ሰዎችን የጫነችው ባለሞተር ጀልባ “ወዲያው መስመጧን” አቶ ፍጹም አስረድተዋል።
አደጋው መከሰቱ እንደታወቀ የተጎጂዎችን ህይወት ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም፤ በጫሞ ሐይቅ ላይ በነበረው ከፍተኛ ማዕበል ምክንያት አለመሳካቱን የጽህፈት ቤት ኃላፊው አመልክተዋል። “ከአደጋው መድረስ በኋላ ከአርባ ምንጭ ከተማ በመጡ ዋናተኞች ጭምር ሕይወት ለማዳን ቢሞከርም፤ ነገር ግን በሰዓቱ የነበረው ማዕበል አላስቻለም” ብለዋል።
በጫሞ ሐይቅ ላይ የነበረው ማዕበል ዛሬ ጠዋት “ጋብ” ማለቱንም አክለዋል። የሟቾችን አስክሬን ለማግኘት ዛሬ ጠዋት በተካሄደው ፍለጋ፤ የሁለት ሰዎች አስክሬን በሐይቁ ዳርቻ መገኘቱን እና ፍለጋው አሁንም መቀጠሉን አቶ ፍጹም ገልጸዋል።
