

በተቋሙ ውስጥ እየተስተዋለ የሚገኘው ከፍተኛ ሙስና ቅሌት በተመለከተ ግልጽ መግለጫ እንዲሰጥና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ የተቃወሞ ሰልፍ በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ መምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
በነገው ዕለት የሚካሄደው የተቋውሞ ሰልፍ አስተባባሪ የሆኑ ከመምህራንና ከአስተዳደር ሰራተኞች የተወጣጡ “ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ” ባደረሱት መረጃ ዩንቨርስቲው ትውልድ የሚቀረፅበት ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ሌብነት እየተፈፀመ ቢገኝም የሚመለከተው አካል በጥፋተኞቹ ላይ እርምጃ አለመወሰዱ ለዚሁ ሰልፍ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፈው ወር የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ላይ በርካታ የኦዲት ግኝቶች መገኘቱን ተከትሎ በአስር ቀናት ውስጥ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ተወስዶ ሪፓርት እንዲደረግ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ትዕዛዝ ቢሰጥም እስካሁን ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱ እጂግ የሚያሳዝንና የህግ የበላይነት በዩንቨርሲቲው አለመኖሩን የሚያሳይ በመሆኑ በነገው ዕለት ሁሉም ሰራተኞች በአደባባይ የተቋውሞ ሰልፍ ለመውጣት የተገደዱት ስሉም አክለው አስረድተዋል።



ሰሞኑን አንድ የዩንቨርሲቲው የማህበረሰብና ስነሰብ ኮሌጅ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አብራሃም ከበደ የተባሉ ግለሰብ ህጋዊ ክፊያ በማጭበርበር በእናት፣ እህት፣ ወንድምና ቅርብ ዘመድ ስም በአንድ ቀን ከዩኒቨርስቲው በጀት ከአንደ ነጥብ ግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በግል አካውንታቸው እንዲገባ የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ይፋ ቢወጣም ዩንቨርስቲው በጉዳዩ ዙሪያ ምንም አይነት አስተያየት አለመስጠቱ ህገወጥ መሆኑን ለመግለጽም ጭምር መሆኑንም የሰልፉ አስተባባሪዎች አስረድተዋል።






በተቃራኒው “የዩንቨርስቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች ለስራ የተመደበው ገንዘብ በህገወጥ መንገድ በግለሰቦች እየበዘበዘ በህጋዊ መንገድ ለሰሩት ስራ በጀት የለም እየተባለ በርካቶች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እየደረሰ ከመሆኑም በላይ ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑ አሳዛኝ ነው” ብሏል።
በመሆኑም በነገው ዕለት ይሄንን በዩንቨርሲቲው እየተደረገ የሚገኘውን እጂግ አሳፋሪና ህገወጥ ተግባር ለመላው ሀገሪቱ ህዝብና መንግስት ለማሰማት የሚደረግ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሁሉም የዩንቨርስቲው መምህራንና አጠቃላይ አስተዳደር ሰራተኞች መደበኛ ስራ ስለማይኖር መብታቸውን ለማስከበር እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።