

ከዎላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ የሕግ ጥሰት ጋር በተያያዘ 93 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ።
የፍትህ ሚኒስቴር እና ፌዴራል ፖሊስ ዛሬ በጋራ በሰጡት መግለጫ÷ ምርጫ ቦርድ የዎላይታ ዞን ድምፅ ውጤት ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ የተፈፀሙ የሕግ ጥሰቶች ላይ ምርመራ ሲደረግ መቆየቱ ተመላክቷል፡፡
በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ሃላፊ ሙሊሳ አብዲሳ÷ከ451 ከሚሆኑ ግለሰቦች በተገኘው መረጃና የሰነድ ማረጋገጫ 136 ተጠርጣሪዎች መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ ውስጥ 18ቱ አመራሮች ሲሆኑ ÷118ቱ ደግሞ የምርጫ አስፈፃሚዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እስካሁንም 18ቱ አመራሮች እንዲሁም 75ቱ ምርጫ አስፈፃሚዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የገለጹት፡፡
በተደረገው ምርመራ የተሰሩት ወንጀሎች መራጮች ድምፅ ባልሰጡበት ኮሮጆዎችን መሙላት፣ ያልተመዘገቡ መራጮችን ማካተትና የምርጫ ምልክቶችን ሳይሞሉ መቅረት መሆናቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።
የህግ ጥሰቱ በዞኑ በ14 ወረዳዎች ላይ የተፈፀመ ሲሆን÷ ምርመራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ፀጋ ተናግረዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ምበደ/ብ/ብ/ሕ ክልል ሥር በሚገኙ 6 ዞኖችና 5 ልዩ ወረዳዎች ላይ ህዝበ ውሳኔ ማካሄዱ የሚታወስ ሲሆን÷የዎላይታ ዞን ውጤት በሕግ ጥሰት ውድቅ ተደርጓል ስል ኤፍቢሲ ዘግቧል።