የዎላይታ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎህነን) በሀገራዊ ፓርቲነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የመስራች ጠቅላላ ጉባኤ በነገው ዕለት እንደሚያካሂድ ተገለፀ።

የዎላይታ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ያገኘው ከአራት ወራት ገደማ በፊት ነበር።

ዎህነን ጊዜያዊ ፈቃዱን ካገኘ በኋላ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ በአምስት ክልሎች እና በአንድ የከተማ አስተዳደር የመስራች አባላትን ፊርማ ሲያሰባስብ መቆየቱን ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፓርቲው በትግራይ፣ አፋር ፣ ኦሮሚያ፣ ቀድሞ ደ/ብ/ሕ/ክልል፣ ጋምቤላ ክልሎች እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 13 ሺህ ገደማ ፊርማ ማሰባሰቡን የፓርቲው አደራጆች ለ“ለዎላይታ ታይምስ” ተናግረዋል።

ንቅናቄው ዋና አላማ በጠንካራ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እና በዎላይታዊ ማንነቱ የማይደራደረው የዎላይታ ሕዝብ ከ፸ በመቶ የሚልቀዉ አሁን ዎላይታ ተብሎ ከሚጠራው አከባቢ ውጪ የሚኖረዉ የህዳጣን መብት እንዲከበርለት፣ በሀገሪቱ በተለይም በአከባቢው ያለው ህዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ፓለቲካዊ መብቶች እንዲጠበቁ በግለሰብ ደረጃ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በተደራጀ ሁኔታ ለመስራት እንዲያስችል የተመሰረተ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም ንቅናቄው ሁሉአቀፍ ተሳትፎ በማረጋገጥ እውነተኛ ለውጥ እንዲመጣ በተሻለ አደራጃጀት ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱንም በላከልን መረጃ አሳውቋል።

በአከባቢው ተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች ላይ የተለያዩ ጫናዎች በገዢው ፓርቲ የሚደርስ ቢሆንም ይሄንን ጫና ተቋቁሞ ለህዝብ ነፃነትና በሀገሪቱ በሁሉም ዘርፍ እኩል ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በሙሉ አቅም በውጭ ሀገርና ሀገርውስጥ የሚገኙ ለህዝብና ለለውጥ ተቆርቋሪ የሆኑ ግለሰቦች ጥምረት ለመንቀሳቀስም ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ንቅናቄው ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጠቁሟል።

የዎላይታ ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ዎህነን) በሀገራዊ ፓርቲነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የመስራች ጠቅላላ ጉባኤ በነገው ዕለት በዎላይታ ጉተራ አዳራሽ ከስድስቱም ነባር ክልሎች የመስራች ጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች፣ የክብር እንግዶች እንዲሁም የተለያዩ ሚዲያዎች በተገኙበት እንደሚያካሂድ ተገልጿል።
ጠንካራ ህብረብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓት ለጠንካራ ሀገር ግንባታ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: