

የዎላይታ ህዝብ ህገመንግስታዊ በክልል የመደራጀት መብት ጥያቄ ተጨማሪ ገንዘብና ጊዜ ሳይባክን ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ ተገለፀ።
የመብት ተሟጋችና የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አሸናፊ አብራሃም ከአዲስ ኮምፓስ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ “የዎላይታ ህዝብ በህገ መንግስቱ መሰረት በራሱ ህጋዊ ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ ወሰነው የነበረው ውሳኔ ባልተወከሉ ተወካዮች ተሽሮ የተደረገው ህዝበውሳኔ በህዝቡ ተቀባይነት ባለማግኘቱ መሰረዙን ተከትሎ ጥያቄው ተጨማሪ ገንዘብና ጊዜ ሳይባክን እንዲሁም መስዋዕትነት ሳያስከፍል ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“ገዢው ፓርቲ ህዝቡ በፍጹም ሰላማዊ መንገድ የሚያካሂደውን ትግል ማበርታታት ሲገባው በተለያዩ መንገዶች ለማፈን የሚያደርገውን ማንኛውንም አካሄድ በማቆም የዎላይታ ህዝብ በሀገሪቱ እኩል ተጠቃሚነትን እንዲጎናጸፍ የሚጠይቀውን ህጋዊና ፍትሀዊ ጥያቄው ምላሽ በአስቸኳይ መስጠት አለበት” ስልም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በዎላይታ ዞን የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ምርጫ ውጤት በተፈጠረው “መጠነ ሰፊ” ጥሰቶች ምክንያት ውድቅ አድርጎ በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑ መወሰኑን ያደነቀው የመብት ተሟጋቹ በህዝቡ ዘንድ ያለውን እውነታ ሳይረዳ አሁንም የሚደረግ ምርጫ አላስፈላጊ ጊዜና ገንዘብ የሚባክን በመሆኑ እውነተኛ የህዝብ ፍላጎት በምርጫ አማራጭ ላይ እንዲካተት ጠይቋል።
የዎላይታ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ የመልማት ጊዜውን በመዋቅር ትግል ብቻ እያደረገ በመሆኑ መንግስት ገንዘብ ሳያባክን በፖለቲካ አቅጣጫ በአስቸኳይ የህዝቡን እውነተኛ ፍላጎት እንዲያከብርና እንዲያስከብርም የመብት ተሟጋቹ ጥሪ አቅርበዋል።
በተቃራኒው መንግስት ተገቢ ምላሽ መስጠት ሲገባው የህዝቡን ራሱን በራሱ የማስተዳደር የማይገረሰስ መብት ለመቀልበስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የማያቆም ከሆነ መላውን ህዝብ ያሳተፈ የተደራጀ ትግል እንቅስቃሴ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በአከባቢው ለህዝብ የሚወግኑ የመብት ተሟጓቾችን የማሰር፣ ከስራ የማፈናቀል፣ የተለያዩ ጫና የመፍጠር፣ አመራሮችን ከየመዋቅሩ የማሳደድና ህዝብ ባላመነበት ለመተካት የሚደረገው ጊዜያዊ ሩጫ ቆሞ የዎላይታ ህዝብ ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ የሆነው “የዎላይታ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት” በአስቸኳይ ምላሽ መሰጠት እንዳለበትም አስረድተዋል።
የዎላይታ ህዝብ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የራሱን ጉዳይ በራሱ ለመወሰን የሚያደርገው ትግል ከኢትዮጵያ አንድነት ጋር የማይጣረስ በመሆኑ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ከዎላይታ ህዝብ ጎን እንዲቆሙ ስልም የመብት ተሟጋችና የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አሸናፊ አብራሃም ከአዲስ ኮምፓስ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአፅንኦት ጠይቋል።
