የቁጫ እና የዛይሴና ሌሎች ሕዝቦች አቤቱታ

በኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልል ም/ቤት የቁጫ ምርጫ ክልል ሕዝብ እና የዛይሴ ምርጫ ክልል ተወካዮች ወቅታዊ የአካባቢያቸውን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እየደረሰብን ያሉትን የአስተዳደር በደል እንዲሁም የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች ይፋ አደርጓል።

በቁጫ እና በዛይሴ አካባቢዎች ምርጫ 2013 ዓ.ም ውጤትን መነሻ በማድረግ “ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን መርጣችኋል” በሚል በሁለቱም ምርጫ ክልሎች ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለው ሕገመንግሥታዊ ጥሰት እንዲቆም መንግሥት የሕግ የበላይነትን ያስከብር ዘንድም ጥያቄ አቅርበዋል።

መግለጫውን የሰጡት ረ/ኘሮፌሰር ገነነ ገደቡ ከቁጫ ምርጫ ክልል፣ አቶ አብርሃም አሞሼ ከዛይሴ ምርጫ ክልል እንዲሁም የመቶአለቃ ማሴቦ ማዳልቾ እና አማኒያስ ጉሽና ናቸው።

በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል የቁጫ እና የዛይሴ ሕዝብ ያለፈውን የምርጫ ውጤት ተከትሎ በመንግሥት መዋቅር የታገዘ ጥቃት፣ ለልዩ ልዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጋለጡን ተናግረዋል። በአካባቢዎቹ ሰዎችን ያለምክንያት ማሰር፣ ማሳደድ፣ ማዋከብ፣ ንብረት መቀማት፣ ከሥራ ማፈናቀል ከመድረሱም በተጨማሪ ሕዝቡ የደህንነት ስጋት እንደተደቀነበት ተናግረዋል።

በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎችን አቅፎ አዲስ ክልል ለመመስረት በተካሄደው ሕዝበ ውሣኔ ላይ እንዳይሳተፉ በርካታ ሰዎች የመራጭነት ካርድ መከልከላቸውን፣ አማራጭ እየቀረበ አለመሆኑን እንዲሁም ገለልተኛ ምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ታዛቢዎች በሌሉበት ሁኔታ የሚካሄድ መሆኑን በመጥቀስ ሒደቱን አጣጥለውታል።

ረ/ኘሮፌሰር ገነነ እንዳሉት አብዛኛው የቁጫ ሕዝብ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን መርጠሃል ተብሎ እንዲፈናቀል፣ እንዲሰደድና እንዲታሰር ተደርጓል ያሉ ሲሆን ጥቃቱ በአዲስአበባ የሚገኙ የአካባቢው ተወላጃች ላይ ጭምር ያነጣጠረ ነው ብለዋል።

አቶ አብረሃም በበኩላቸው ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የዛይሴ ብሔረሰብና ሕዝብ የወረዳ እና የዞን አስተዳደራዊ መዋቅር ይፈቀድልን ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ የአካባቢው ሕዝብ (የሀገር ሽማግሌ፣ ሕጻናትና ሴቶች ሳይቀር) እጅግ አሰቃቂ የጅምላ ድብደባ፣ እስር፣ ማሳደድና ማፈናቀል ወንጀል በአካባቢው የአስተዳደር አካላት ተፈፅሞባቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በጋሞ ዞን ውስጥ የዛይሴ፣ የጊዲቾ እና የጋሞ እና ሌሎችም ብሔር ብሔረሰቦች ባሉበት ሁኔታ ሶስቱንም የማይወክል የዞን ስያሜ መኖሩ የአንድ ብሔረሰብ የበላይ እንዲሆን አድርጓል በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በቁጫ እና በዛይሴ ሕዝብ ላይ እየደረሰ የሚገኘው የአስተዳደር ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ በደሎች በአስቸኳይ ይቀረፉ ዘንድ የፌደራል እና የክልሉ መንግሥታት የሕዝባችንን ቅሬታ ይስሙልን ሲሉ ተማፅኖአቸውን አቅርበዋል ስል ድሬቲዩብ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: