የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም ዎላይታ ውስጥ በሕዝብና በሕግ ተቀባይነት የለለውን የፖለቲካ ውሳኔ ምርጫ ለማካሄድ ማቀዱ ይታወቃል።

ምርጫውን የሚያስፈጽሙ አካላትን በሚመለከት ባወጣው መረጃ ከ5,412 በላይ አስፈፃሚዎችን ከአዲስ አበባ በማምጣትና 3,608 ከዎላይታ በመልመል “ተሰርቋል” ያለውን ምርጫ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሠላማዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑ ተብራርቷል።

ማስተባበሪያ ማዕከላትንከ8 ወደ 11 ማሳደጉም የተገለፀ ስሆን ተጨማሪ 692 ምርጫ ጣባያዎችን ለመክፈት ማቀዱም ይታወቃል።

በአንድ ጣቢያ ድምፅ የሚሰጥ መራጭ ቁጥር 1,500 ከነበረበት ወደ 800 ዝቅ በማድረግና የአስፈጻሚዎችን ቁጥር ከ5,560ከነበረበት ወደ 9,020 በማሳደግ ምርጫውን በአንድ ቀን ማለትም ከጧት 12:00 ሰዓት እስከ ምሽት 12:00 ለማጠናቀቅ ማቀዱን ማድረጉ ይታወሳል።

የዞኑ ብልፅግና ሹማምንት የሚዘውሯቸው የቀድሞ ምርጫ አክፈሚዎች 998,800 ዎላይታውያን በምርጫው ይሳተፋሉ ማለታቸውና ምርጫ ቦርድም ይህን አሃዝ በወቅቱ ይዞ መውጣቱ የሚታወስ ስሆን “በድጋሜ አካሂዳለሁ” ባለውም ምርጫ የጠቀሰው ቁጥር ያለው ሕዝብ ድምፅ ለመስጠት ይችላል የሚል ግምት ቦርዱ አስቀምጧል።

ይሁን እንጂ “ምርጫ ቦርድ 998,800 ሕዝብ በ12:00 ሰዓታት ውስጥ ተቀብሎ ማስተናገድና እቅዱን በፍፁም ውጤታ ማድረግ አይችልም” የሚሉ በርካቶች “እቅዱን ካለማሳካት ባሻገር ቦርዱ ዎላይታ ላይ ለመጫን የሚፈልገው አንዳች ነገር አለ” ይላሉ።

የቦርዱ እቅድ ለምን አይሳካም?

ቦርዱ ከጧት ሰዓት12:00 እስከ 12:00 ሰዓት ያለውን ጊዜ ተጠቅሞ “በአንድ ቀን ምርጫውን አጠናቅቃለሁ” ያለው ሰዓታት ወደ ደቁቃዎች ስሸነሸኑ 720 ደቂቃዎች ናቸው።

አንድ ግለሰብ ምርጫው ላይ ለመሳተፍ የሚያስችልና ማንነትን የሚገልፅ ሕጋዊ መታወቂያ በማሳየት ይመዘገባል። ከተመዘገበ በኃላ ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን ካርድ ተመዝግቦ ይወስዳል። ካርድ ከወሰደ በኃላ እንደገና ተሰልፎ በመመዝገብ ለምርጫው የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ይወስዳል። በመጨረሻም “ሚስጢር ይጠበቃል” የሚባልበት ክፍል ውስጥ ገብቶ ድምፅ በመስጠት የዕለቱን ተግባር ያጠናቅቃል።

ሂደቱ እጅግ የዘመነና ቀልጣፋ ነው ብባል እንኳን አንድ ግለሰብ ከላይ የተሰቀሱ ሁሉንም ሂደቶች አልፎ ድምፅ ሰጥቶ ለመውጣት ከ7 -10 ደቂቃ ይፈጅበታል። በተጨማሪ የተለያዩ ምርጫውን የሚያስተጓጉሉ ሁኔታዎችና በአስፈጻሚዎች ብቃት ውስንነት የሚባክን ጊዜ የለም ማለት አይቻልም።

ታዱያ በአንድ ምርጫ ጣቢያ 800 መራጭ ድምፅ እንዲሰጥ ቦርዱ ባስቀመጠው መሠረት ብናሰላና አንድ ግለሰብ በትንሹ ሰባት(7) ደቂቃ ይጠቀማል ብባል እንኳን በቂ ያልሆነ ጊዜ ነው።

የአስፈጻሚዎችን ድጋፍና እርዳታ የሚፈልጉና ጊዜ በአግባቡ መጠቀም የማይችሉ መራጮች መኖራቸውም ግልፅ ነው። በዚህም ድምፅ መስጠት ከሚገባቸው 800 መራጮች ከ150 በላይ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ ያደርጋል። በመሆኑም በዚህ አካሄድ ምርጫው በፍፁም ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

የምርጫ ቦርዱ ዓላማ ምንድን ነው?

ካለፈው ኢህአዴግ ጊዜ ጀምሮ ሐገራዊ ምርጫ ስካሄድ የነበረው በተለመደው ስርቆትና በማጭበር መሆኑ፣ አሁን ያለው ብልፅግናም በዚያ መንገድ እድሜውን ያራዘመ መሆኑ፣ ሐገሪቷ ውስጥ የሚካሄደው የትኛውም ምርጫም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ በተለመደው ሊጓዝ እንደሚችል እየታወቀ፣ ዎላይታና ሌሎች ደቡብ ክልል አከባቢዎች የተካሄደው ሕዝበ ውሳኔም ሐገሪቷ የመጣችበትን መንገድ ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑ እየታወቀ፣ ምርጫ ቦርድ የዎላይታን ብቻ መርጦ “ሕገወጥ ነው” ያለበት “ምክንያትና ዓላማው ምንድን ነው?” የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድ አከባቢ ሰዎች እንደተሞላ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ። በተለይ ከሰሜኑ አከባቢ የተሰባሰቡ መሆናቸውን በግልፅ ይናገራሉ። እነዚህ አካላት በዎላይታ ሕዝብና ጉዳይ ላይ የተንሸዋረረ ዕይታና አሉታዊ ፍላጎት ያላቸው እንደሆኑም ይታማሉ። ዎላይታ ሕዝብ ክልል እንዳይሆንም “በህቡዕ ተደራጅተው ይሰራሉ” በሚል የሰላ ትችና ወቀሳ ይደርስባቸዋል።

ታዱዲያ እነዚህ አካላት ብልፅግና አደራጃለሁ ያለው ክልል ማዕከል አርባምንጭ እንዲሆን ይፈልጋሉ። አርባምንጭ ለመውሰድ ደግሞ በዎላይታ ያለው መራጭ ሕዝብ ቁጥር በማንመን በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ተገቢውን ውጤት እንዳያገኝ ማድረግ ነው።

ለዚህም ምዝገባውን፣ ካርድ መውሰድና፣ ድምፅ መስጠትን አንድ ቀን ውስጥ በማድረግ በወከባ ሁሉም መራጭ እንዳይሳተፍ ማድረግ ሁነኛ መንገድ ነው። በተለይ በእያንዳንዱ ጣቢያ ከ200 በላይ ሰው ድምፅ እንዳይጥ በማድረግ ከሁሉም ጣቢያዎች ከ360,800 በላይ መራጭ ከምርጫው ውጭ ማድረግ ብቸኛው ዓላማቸው ነው።

ይህ ስሆን ጋሞ ዞን ውስጥ አለ ተብሎ ከሚገመተው መራጭ ሕዝብ ቁጥር ዎላይታን እኩል ማድረግና በተቀመጡ መስፈርቶች ተወዳዳሪ ሆኖ እንዳይጣ ማድረግ የመጨረሻ ግባቸው ነው። በዚህም ያለሙት ተሳክቶ ማዕከሉ አርባምንጭ ስሄድ የፈለጉትን ውክልና መዋቅር እዚያው ዘርግተው አሃዳዊነትን እንደልብ መስበክና ማስረፅ ነው።

የዎላይታ ሕዝብ ለማዕከል ይፎካከራል?

የዎላይታ የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ስጠየቅና ትግል ስደረግበት የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ስሆን በእነዚህ ትግል ዓመታት ሁሉ አንድም ቀን “የአስተዳደር ማዕከል ይሰጠኝ” ጥያቄ አሰምቶ አያውቅም።

በተለይ አሁን ኢትዮጵያ የሚትመራበት ሕገመንግሥት በአንቀፅ 47 ስር ባሰፈራቸው አንቀፆች አንድ ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ ለመወሰንና ብቻውን ለመደራጀት መጠየቅና መታገል እንደሚችል በግልፅ ደንግጓል።

በመሆኑም ሕግ የሚያጎናፅፈውን መብት ተጠቅሞ፣ ከሌሎች ጋር በጋራ ክልል መጠየቅ እንዲችል የሚያደርግ አሰራር አለመኖሩን በመገንዘብ

  1. ስያሜው ዎላይታ ብሔራዊ ክልል የሆነ፣
  2. መቀመጫውን ዎላይታ ሶዶ ያደረገ፣
  3. የሥራ ቋንቋው ዎላይታቶ የሆነ፣
  4. ሰንደቅዓላማው በቀይ፣ በብጫና በጥቁር ቀለማት ያሸበረቀ፣
  5. በራሱ በዎላይታ ሕዝብ ብቻ የሚመራና የሚተዳደር ነፃ ክልል በይፋ ጠይቋል።

ምርጫ ቦርድ በዎላይታ ዞን የመጀመሪያውን ህዝበ ውሳኔ በከፍተኛ ህግ ጥሰት ምክንያት ከሰረዘ በኃላ በድጋሚ ሰኔ 12/2015 ዓ.ም ለማካሄድ ይፋ ማድረጉ ተከትሎ የዎላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ባወጣው መግለጫ “በድጋሚ ቀጣይ የሚካሄድ ህዝበ ውሳኔ የዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሚል አማራጭ ያልተካተተ ከሆነ ፓርቲያችን ለኢ-ህገመንግስታዊ ሪፈረንደም እውቅና የማይሰጥ መሆኑን ከወድሁ እናሳውቃለን” ስል መግለፁ ይታወሳል።

በተመሳሳይ መንገድ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ “ዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት” የሚል አማራጭ በድጋሚ ምርጫ ላይ እስካልቀረበ ድረስ ለህዝበ ውሳኔ ህጋዊ እውቅና እንደማንሰጥ እና ሂደቱንም ውጤቱንም እንደማንቀበል በአፅኦት አሳውቀን ወጥተናል” በሚል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ማሳወቁም የሚታወስ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: