

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል በዎላይታ በድጋሚ ለማካሄድ በቀረቡ የምርጫ ምልክቶች በርካቶችን እያወዛገበ በመሆኑ ተጠይቆ ምላሽ ሰጥቷል።
በደቡብ ክልል “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የሚል አዲስ ክልል ለማዋቀር ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች በጋራ ለመደራጀት ጥር 29/2015 ዓ.ም ባካሄዱት ህዝበ ውሳኔ የቀረቡ የእርግብ እና ጎጆ ምልክቶች በማያሻማ መንገድ የተቀመጡ ስለመሆኑ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ
ከቦርዱ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ቦርዱ በጥር 29/2015 ዓ.ም ሆነ በዎላይታ ላይ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በህግ ጥሰት ምክንያት ከተሰረዘ በኃላ በድጋሚ የቀረቡ ምልክቶች በተለይም የጎጆ ምልክት “ከአገላለፅ ልዩነት በስተቀር በደቡብ ክልል ከዚህ በፊት በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምርጫ ወቅት ነባሩን ክልል በመወከል የቀረበ ምልክት ነው” በሚል አስረድቷል።
ቦርዱ ለምርጫ የቀረበው ምልክቱ አሻሚ እንዳይሆን ተፈልጎ ላም ተብሎ የቀረበውን ፌደሬሽን ምክርቤቱ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መስተዳድር ዐርማ የሆነው ጎጆ ቤት እንዲሆን ጥያቄ በማቅረቡ፤ ቦርዱም የምክር ቤቱን ጥያቄ ተቀብሎ ስድስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች በአንድ የጋራ ክልል መደራጀታቸውን አልደግፍም ለሚለው የሕዝበ ውሣኔ አማራጭ ሃሣብ ምልክት ጎጆ ቤት እንዲሆን መወሠኑን በይፋ በወቅቱ በማያሻማ መንገድ መግለፁንም ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።
መራጩ ህዝብ በግልጽ የተቀመጡ የምርጫ ምልክቶችን በመጠቀም ለራሱ ይበጃል የሚለውን በመምረጥ ያለምንም መወዛገብ ተሳትፎ እንዲያደረግ ቦርዱ ጥሪ አድርጓል።