

በዎላይታ ሰኔ 12 ይካሄዳል በተባለው ዳግም ሕዝበ ወሳኔ ቅስቀሳ ወቅት ከፌደራልና ከክልል የመጡ የአከባቢው ተወላጅ አመራሮች ጫና ያቃታቸው አንዳንድ አመራሮች ኃላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው እየለቀቁ እንደሚገኙ ከታማኝ ምንጮች መረጃ ለማግኘት ችለናል።
ለአብነት በዳሞት ሶሬ ወረዳና በጉኑኖ ከተማ አስተዳደር አከባቢ ከነበሩ አመራሮች አንዳንዶቹ እንዲሁም ከሌሎች መዋቅሮች በገዛ ፈቃዳቸውን ሥልጣን እየለቀቁ መሆኑን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የደረሰው መረጃ ይጠቁማል።
ልዩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ለአሥራ አምስት ቀናት ወደ ታች የተላኩት የዞንም የወረዳና የቀበሌ አመራሮች ምንም ዓይነት የመንግስት ሥራ ሳይሰሩ ሕዝቡ የግልም የመንግስት ሥራዎች በአገባቡ እንዳይከናወን ከማደናቀፍ በላይ ምንም ነገር ባልተመቻቸበት ሁኔታ ጫና እየፈጠሩ እንደሚገኝ መረጃው ደረሶናል።
ይህ በንዲህ እንዳለ አመራሩ ሕዝቡን በምርጫ እርግብ ካላስመረጣችሁ በአመራርነት መቀጠል ስለማትችሉ ለእንጀራችሁ ሥሩ ተብሎ ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠታቸው ተስፋ ቆርጠው የወፏን ምስል ተሸክሞ በየማህበራዊ ሚዲያ ከመለጠፍ ባለፈ ለሕዝቡ ተስፋ ሰጪ ነገር እየሠሩ እንዳይደለ አመራሮች ራሳቸው የሚያምኑት ጉዳይ እየሆነ መጥተዋል።
አንዳንድ አስተያየት ከሚሰጡ ማህበረሰብ ክፍሎች ባገኘነው መረጃ መሠረት ለመምረጥ በግዴታ እስከሆነ ድረስ ሁለቱን ዋጋ ማሳጣት ወይም ጎጆ እንመርጣለን እያሉ ይገኛሉ።
አመራሮች በተለይ በወረዳም ሆነ በዞን ደረጃ በአስፈጻሚ አመራር ቦታ የሌሉት እጅግ በጣም ተጨንቀውና ሥልጣናቸው እንዳይቀማ ሥጋት ገብተው ስምሪቱን እያከናወኑ እንደሚገኙ የደረሰው መረጃ ያረጋግጣል።
በሌላ በኩል “ህዝበ ውሳኔ” ምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ የአከባቢው አመራሮች ምርጫ መቀስቀስ በህግ በማይቻልበት የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን፣ በጤና ተቋማት ላይ፣ የሞተር አከራዮችንና ሌሎች ህብረተሰብ ክፍሎችን በተለያዩ መንገዶች በማስፈራራት “እርግብ ምረጡ” የሚል ቅስቀሳ እንዲያደርጉ እያስገደዱ ይገኛሉ።
ዎላይታ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም አመራሮችች መደበኛ የመንግስት ስራ በማቆም ቅድመ ምዝገባ በሚል ለቤት እየገቡ የዜጎች ዴሞኪራሲያዊ መብታቸውን በመጣስ 1ለ 10 የሚል ህቡዕ አደራጅቶ “እርግብ ምረጡ ወይንም ጎጆ ምረጡ እኛ የምንፈልገው ህዝብ ቁጥር እንዲወጣ ነው፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መመስረት በመንግሥት የተቀመጠ አቅጣጫ ነው” እያሉ ነዋሪዎቹን እያስገደዱ እንደሆነም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።




በትናንትናው ዕለት የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ እና የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በዎላይታ ህዝብ ላይ ህገመንግስትን በሚፃረር መንገድ እየተፈፀመ ያለ አፈናና ኢ-ህገ መንግስታዊ “ህዝበ ውሳኔ” በህግ እንዲሻርና እንዲታገድ በፈደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱን እንዲሁም ሁኔታውን ለተለያዩ ኤምባሲዎችና ጉዳዩ የሚመለክታቸው አካላት በሙሉ እያደረሱ ስለመሆኑ መዘገባችን ይታወሳል። በሪፓርተር ናትናኤል ጌቾ

