

ኢትኪውብል የተባለው የፈረንሳይ የቡና ተረካቢ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጉሌማን የዎላይታ ቡና ጥራትና ተፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና ገልጸው ቀጣይ ቡናው ከዚህ የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚያስተዋወቁ ተናግረዋል።
ኩባንያው በዚህ ብራንድ የዎላይታ ቡና በተሻለ ሁኔታ እንዲታወቅ ከማድረግ ሥራ ባሻገር በተቋማቸው ቡናውን እሴቱን በመጨመር ውጤታማነቱን የማረጋገጥ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ሚስተር ጉሌማን የገለጹት።
የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ እንደዘገበው በቅርቡ የራሱን ብራንድ ስያሜ ያገኘው የዎላይታ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭነቱና ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዎላይታ ሶዶ ቅርንጫፍ የቡና ቅምሻ ማዕከል ሶስት ዓይነት አገልግሎት ከሚሰጡት ውስጥ የምርቶች ጥራት ደረጃ ምደባ ሥራ፣ የመጋዘን አገልግሎት እንዲሁም ሻጭና ገዥውን የማገናኘት አገልግሎት እየሰራ እንደሚገኝ የቡና ጥራት ቁጥጥር ሱፐርቫይዘር አቶ አብነት አሻ ገልጸዋል።



አቶ አብነት እንዳብራሩት የዎላይታ ቡና በታጠበና በቅሽር የተዘጋጀ ቡና በሀገር ወስጥና በዓለም ገበያ ላይ ተወዳጅነቱ እየጨመረ መምጣቱ በቀጣይ ጊዜ ለሚኖረው አቅርቦት አቅም መሆኑን ጠቁመዋል።
በወላይታ ሶዶ ቡና ቅምሻ ማዕከል የጥራት ደረጃ ክትትል ክፍል ቡና፣ ጥራጥሬ ማለትም ሰለጥ፣ አረንጓዴ ማሾ፣ የተለያዩ ቦለቄ ዘር ዓይነቶች፣ የእርግብ አተር የመሳሰሉትን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አቶ አብነት ጠቁመዋል።
ወደ ማዕከሉ የሚቀርቡ የቡናና ጥራጥሬ አቅርቦት ከዎላይታ፣ ከከምባታ ጣምባሮ ፣ ከሃዲያ ፣ሃላባ፣ ከጋሞ ጎፋ፣ ከደቡብ ኦሞ፣ ከኮንሶ ዞኖች ጨምሮ ሌሎች አጎራባች ክልል ዞኖች በማዕከሉ እየተገለገሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።