

ዎላይታ ሶዶ ከተማን የአስተዳደርና የፓለትካ ማዕከል አድረገው የሚመሰረተው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ይፋዊ የምስረታ በሳምንቱ መጨረሻ በአርባ ምንጭ ከተማ ሊያደርግ ነው።
የነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤትም በተመሳሳይ ወቅት አስቸኳይ ጉባኤ መጥራቱን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ተናግረዋል። በአርባ ምንጭ ከተማ የሚካሄደው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ምስረታ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑን የጋሞ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ኤደን ንጉሴ ገልጸዋል።
ከነገ በስቲያ አርብ ነሐሴ 12፤ 2015 በሚኖረው መርሃ ግብር፤ የአዲሱ ክልል ምክር ቤት መስራች ጉባኤውን እንደሚያደርግ ኃላፊዋ አስረድተዋል። በዚሁ ጉባኤ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የአዲሱን ክልል ህገ መንግስቱን ተወያይተው ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
በማግስቱ ቅዳሜ ደግሞ 12ኛው የፌደሬሽኑ ክልል በይፋ የምስረታ ፕሮግራሙን እንደሚያካሄድ ኤደን ጠቁመዋል። የአዲሱ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የካቤኔ አባላትም በዚሁ ቀን ይሾማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዋ አክለዋል ስል ኢትዮጵያ እንሳይደር ዘግቧል። Wolaita Times