

“አዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተባለው የብሄረሰቦችን ማንነት በማፈን ስራውን ጀመረ” ስሉ የቁጫና የዘይሴ ብሄረሰብ አባላት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ማዕከላዊ ደቡብ ኢትዮጵያ “የዘመናት ማንነት ጥያቄ ላላቸው ብሄረሰቦች በየራሳቸው ልዩ ወረዳዎች እንዲተዳደሩ መፈቀዱ ትክክለኛና ወቅቱን የሚመጥን ታሪካዊ ውሳኔ ነው” በሚል መደሰታቸውንም አክለው ገልጸዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም “በጋሞ ዞን ለዘመናት ማንነታቸው ባልወከሉት ታፍነው የቆየው ቁጫ፣ ቦሮዳ፣ ጋንታ፣ ዶርዜ፣ ዘይሴ፣ ካምባ፣ ቦንኬ፣ ኦቾሎ ብሄረሰቦች የልዩ ወረዳና ዞንነት መብት በማፈን ተስፋችንን አጨልሞታል” ስሉ ሁኔታውን በምሬት አስረድተዋል።

የዘይሴ እና የቁጫ ብሄረሰብ አባላት ከዛሬው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ ተከትሎ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት “አሁንም ማንነታችንን በህግ እንዳይከበር በተግባር ሰው መስሎ በስውር ሲያፍኑ ሲጮቁኑ የነበሩ ግለሰቦች ስልጣን ላይ እንዲቀጥሉ መደረጉ መንግስት የማንነት ጥያቄ እንዲመለስ በፌደሬሽን ምክርቤት ያስቀመጠውን አቅጣጫ ለማኮላሸት ምቹ ሁኔታ እንዳያገኙ ሁሉም ማንነቱን የሚወድ ኢትዮጵያዊያን ከጎናችን እንዲሰለፉ” በሚል በአፅንኦት ጥሪ አቅርበዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ላይ ደግሞ “ለዘመናት በጉራጌ እና ካምባታ ዞን ስር የማንነት ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ የጠምባሮ፣ ቀቤና፣ ማራቆ ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተከብሮላቸው በልዩ ወረዳ እንዲደራጁ ምክርቤቱ መወሰኑ ክልሉ ከጅምሩ የማንነት ጥያቄ ላላቸው ምላሽ በመስጠት አብሮ ተከባብሮና ተቻችሎ ለመኖር ለማደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት አኩሪ ውሳኔ በመሆኑ ተደስተናል” ስሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።
ከጅምሩ የብሄረሰቦችን ማንነት መብት ጥያቄ በማፈን የጀመረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 5 ልዩ ወረዳዎችን ወደ ዞን ደረጃ በማሳደግ የዞኖቹን ቁጥር 12 አድርሷል እንጂ በክልሉ የማንነት ጥያቄ ለዘመናት ሲያነሱ የነበሩ በተለይም ለቁጫ፣ ዘይሴ፣ ዶርዜና ቦረዳ ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አለማክበሩ አዲሱ ክልል ከድሮ ሴራኞች እጅ ያልወጣ ፀረ ፈዴራልሲም በሆኑ ሰዎች አስተሳሰብና ሴራ እየተመሰረተ የሚገኝ መሆኑንም የብሄረሰቦች አባላት ተናግረዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህገመንግስት አርቃቂ ኮምሽን አባል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደገለፁት የቁጫና የዘይሴ ልዩ ዞን ጥያቄ በምክርቤቱ እንዲፀድቅ ሁሉም ነገር ካለቀ በኃላ በምን አይነት ሁኔታ መቅረብ እንዳልቻለ አስረድተዋል።
“በተለይም በጋሞ ዞን ለዘመናት ማንነታቸው ታፍነው የሚገኙ የራሳቸው ማንነት ያላቸው ብሄረሰቦች መዋቅር ጥያቄ በክልሉ ብሄረሰቦች ምክርቤት ስብሰባ ላይ የማንነት ጥያቄያቸው ከተመለሰ በኃላ በቀጣይ ምክርቤት ስብሰባ ላይ ሊሆን እንደሚችል” የኮምሽን አባሉ አብራርተዋል።
በተለይም ዛሬ የተዋቀረው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ኃላፊዎች አመራረጥ “ባለፉት ሶስት አመታት በክልሉ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን በህጋዊ መንገድ ያነሱ አመራሮችንና የመብት ተሟጋቾች ከኃላፊነት በሴራ እንዲነሱ ያደረጉ፣ የተለያዩ ስም በመስጠት ያሳሰሩ፣ ከስራ ያፈናቀሉ እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች የህዝብ ጥያቄ እንዲኮላሽ ያደረጉ፥ ውግንና ከህዝብ ይልቅ ለራሳቸው ጥቅምና ፓርቲ ብቻ ያደረጉ፥ በተጨባጭ ሙስናና በብልሹ አሰራር የተዘፈቁ ግለሰቦች እንደወትሮው ተመሳሳይ ስራቸውን እንዲቀጥሉ መፈቀዱ ተገቢና ፍትሀዊ ያልሆነ ውሳኔ በመሆኑ የፈደራል መንግስት በአዲሱ ክልል ለውጥና ልማት እንዲመጣ ከፈለገ በጊዜ ብቃትና የህዝብ ውግንና ያላቸውን አመራሮችን መመደብ አለበት” የሚሉ ድምፅ በየማህበራዊ ሚዲያ እየተደመጡ ስለመሆኑ ያደረግነው የሚዲያ ዳሰሳ ያረጋግጣል።