

ኢትዮ ቴሌኮም የዎላይታ ሶዶ ድስትሪክት ከ10 ዓመት በፊት የድስትሪክቱን ህንፃ ለመገንባት በወሰደው መሬት ላይ ግንባታ አለመጀመሩ ቅሬታ አስነስቷል።
በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ዎላይታ ሶዶ ድስትሪክት በ6 መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ የራሱን ግዙፍ G+11 ህንፃ በሶዶ ከተማ ዲሳይን ወጥቶለት ለብሔራዊ ባንክ ከተሰጠው ቦታ በታች በኩል ዋዱ ቁስቋም ማሪያም ፊትለፍት አንድ ሺህ ካሬ መሬት መጀመሪያ ከ10 ዓመት በፊት ቢሰጠውም እስካሁን ማልማት አለመቻሉ ቅሬታ እየፈጠረ ስለመሆኑ የአከባቢው ነዋሪዎች ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ቅሬታ አቅርቧል።
በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሹሜ አብሽሮ ከህብረተሰቡ ለተነሳላቸው ጥያቄ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በስልክ በሰጡት ምላሽ “ግንባታው መቆየቱን በመግለፅ አሁን ላይ ግንባታውን ለመጀመር ህንፃ በሚያርፍበት ቦታ ላይ ያለው የመሬት ናሙና ጥናትና ተያያዥ ቅድመ ስራዎች እየተሰሩ ነው” ብለዋል።

አቶ ሹሜ የህንፃው ግንባታ በትክክል መች ይጀመራል የሚለው ጥያቄ ቀርቦላቸው “ይሄ ግዙፍ ህንፃ ግንባታ በመሆኑ ጉዳዩን በቀጥታ የፈደራል ኢትዮቴሌኮም የሚመለከት ስለሆነ እነሱም በቅርበት እየተከታተሉ ይገኛሉ” ስሉ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።
የድስትሪክቱ ህንፃ ከመቆየቱም ባሻገር ለግንባታ የተወሰደው መሬት ሳይለማ መቆየቱን ተከትሎ አንዳንድ ጉዳዩን በቅርበት ስከታተሉ የነበሩ ወገኖች ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ “ሌላ ቦታ ሊወስዱት ነው ወይ?” ብለው ያደረሱትን ጥያቄ ለሪጅኑ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሹሜ አብሽሮ ሲናነሳ “ግንባታው ዘግይቷል እንጂ ይሄ በፍጹም የውሸት ወሬ ነው፣ ግንባታው እንዲከናወን የተፈቀደው በፌደራል ዋና መስሪያቤት ኢትዮቴሌኮም ውሳኔ ስለሆነ የሚቀየር አይደለም” ስሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ ሹሜ አብሽሮ ከህዝብ ለተነሳላቸው ጥያቄ ለመመለስ ፍቃደኝነት በማሳየት ለሰጡት ማብራሪያ እናመሰግናለን።
በአሁኑ ወቅት የደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን የሶዶ ድስትርክ ከአስር አመት በፊት ህንፃው እንዲገነባ ከከተማ አስተዳደሩ የተረከበውን መሬት ሳያለማ በግለሰቦች ህንፃ ተከራይቶ እየሰራ ሲሆን በተመሳሳይ ሁኔታ በርካታ ሚሊዮን ገንዘቦችን የሚያንቀሳቅሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶዶ ድስትሪክት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሶዶ ድስትሪክት፣ አዋሽ ባንክ ሶዶ ድስትሪክት፣ የኢትዮጵያ ኤለክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሶዶ ድስትሪክት፣ ብራሃን ባንክ ሶዶ ድስትሪክት፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ሶዶ ድስትሪክት እንዲሁም ሌሎች ትላልቅ ተቋማት በአከባቢው በተመቻቸላቸው መሬት በመውሰድ የራሳቸውን ህንፃ በመገንባት የከተማውን ውበትና እሴት ከመጨመር ይልቅ በግለሰቦች ህንፃ ላይ ክራይ እየከፈሉ ለበርካታ አመታት መቆየታቸው ትክክል ባለመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን።