በአመራሮች መካከል”ክልሉ እውን እንዲሆን በታገልነው ልክ ስልጣን አልተሰጠኝም፤ የህዝብ ውክልናም በተገቢው ተግባራዊ አልሆነም” የሚል የግለሰቦች ፉክክር ከወዲሁ መጀመሩን አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ከፍተኛ አመራር ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።

እንደ የመረጃ ምንጫችን ገለፃ “በነባሩ ክልልና ዞን ውስጥ በተለያዩ ስልጣን እርከን የነበሩና በተለይም ህዝቡ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄ በህጋዊ መንገድ ቀርበው የነበረውን ከህዝብ ፍላጎት ውጪ መንግስት በሰጠን አቅጣጫ መሠረት ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈልና ጫና በማድረግ የክላስተር ክልል እውን እንዲሆን ከፍተኛ ሚና ብንወጣም የሚገባን ስልጣን አልተሰጠንም የሹመት ሂደቱም ያንን ታሳቢ ያላደረገ ነው” የሚሉ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት እርስበርስ መተነኳኮስ መጀመራቸውን አብራርተዋል።

በተቃራኒው አንድ ስማቸውን መግለፅ ያልፈለገና በአዲስ ክልል ሹመት የተሰጠው ከፍተኛ የዎላይታ ተወላጅ የተፈጠረውን ሁኔታ “የዎላይታ ሕዝብ ከክልሉ ብሔሮች ግምባር ቀደም ብዛት ያለው ቢሆንም የገዥ ፖለቲካ ፓርቲ መርነት አልተሰጠውም፤ በሕግ አዉጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ዳኝነት ቦታዎች ላይ የመርነት ቦታዎች አልተሰጡም፤ በክልሉ ጉዳዮች ላይ ዉሳኔ ሰጪ የሚያስብል ቦታዎች የዎላይታ ሕዝብ ዉልክና በትክክል እንዳይኖር ተደርጓል፤ ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው የሕዝብ ዉክልና ማንጸባረቅ ህገ መንግስታዊ ግዴታ መሆኑ እየታወቀ እውነታውን በመጣስ ህዝባዊ መሠፈረትን ያልተከተለ አመራርነት እና ህገ መንግስታዊ መርህን የናደ ሹመት በመስጠት የዎላይታን ሕዝብ አፍኗል፤ የተሾሙ ግለሰቦችም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለላቸው በተለያዩ ጥቅማጥቅም የተሳሰሩ ናቸው፤ በአስቸኳይ የእርምት እርምጃ ካልተወሰደ ክልሉ ገና ሳይመሰረት የመበታተን አደጋ ተጋርጦበታል” ስሉ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።

የአዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በዋልታ ተሌቪዥን መስኮት ቀርበው ተደረገ የተባለውን ሪፈረንደም አስመልክቶ በሰጡት ሀሳብ “ህዝቡ የፈለገውን ነው ያደረግነው” በማለት የገለጸበት መንገድ የዎላይታ ህዝብ ራስን በራስ ለማስተዳደር የከፈለውንና እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ክብር ያለመኖሩን የገለፀበት መሆኑና “የተደራጀው አደረጃጀት የዎላይታን ህዝብ ከወትሮ በበለጠ ለፖለቲካዊና መዋቅራዊ ምስቅልቅል የሚዳርግ ከመሆኑም ባሻገር የዎላይታን ህዝብ ክብርና ታሪኩን የማይመጥን የዜሮ ውጤት ጨዋታ መሆኑን ሁሉም ዎላይታ አውቆ የዎላይታን ህዝብ የሚመጥንና በህገመንግስቱ የተረጋገጠለትን መብት ለማስከበር ህዝባዊና ሰላማዊ ትግሉ አጠናክሮ እንድቀጥል የከበረ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ስሉ አቶ ጎበዜ ጎኣ የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር መግለፃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በሌላ በኩል የጋሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር የአዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሆነው በቅርቡ የተሾመውን ግለሰብ በተመለከተ “ከ2005 ጀምሮ አቶ ጥላሁ ከበደ የጋሞ ጎፋ ዞን ደኢህዴን ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆኖ ዞኑን በሚመራበት ጊዜ ከ2007 ምርጫ ማግስት ማዶላ የተሰኘ መፀሀፍ ታትሟል፣ የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆኖ ያለ ውክልናቸው በጋሞ ዞን ምክር ቤት በመገኘት ድምፅ ሰጥተዋል፣ በደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል በመሆናቸው ድምፅ ሰጥተዋል በመቀጠልም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን በአንድ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ ኢ-ህገመንግስታዊ የሆነ ያለአግባብ በራሱ ጥያቄ አቅራቢ፣ አስፈፃሚ እና ውሳኔ ሰጪ በሌላ አነጋገር ከሳሽ፣ ተከራካሪ እና ዳኛ በመሆን የጋሞ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ጥሰት ፈፅሟል” በሚል ከፍተኛ ትችት አቅርቧል።

“የኛ ቤተሰብ ተበታትነዋል። እኔ በነባሩ ደቡብ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሠራተኛ ስሆን ባለቤቴ ደግሞ በደቡብ ክልል የግብርና ቢሮ ሰራተኛ ናት። ከተጋባን 19 አመታችን ነው። በ19 አመት ውስጥ 4 ልጆች አፍርተናል፣ ሀዋሳ ላይ ቤት አለን፣ ታላቅ ልጃችን 11ኛ ክፍል ተማሪ ነው ሌሎች 8ኛ፣ 6ኛ እና 3ኛ ክፍል ተማሪ ናቸው። በአድሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መዋቅር የክልሉና መቀመጫ ዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ የእኔ መስሪያቤት ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ስላለ እሄዳለሁ፣ ባለቤቴ ድላ ትሄዳለች። የክልሉ መቀመጫ ዎላይታ ይሆናል ብለን ሀዋሳ ላይ ያለውን ቤት ሽጠን ዎላይታ ሶዶ ከተማ ለመምጣት አስብን ተደስተን ነበር። ነገር ግን የክልሉ ቢሮዎች ስበታተኑ ሁሉም ነገር ጨልሞብናል። ልጆቻችን ከማን ጋር ይኖሩ? በዚህ ኑሮ ውድነት በሁለት ቦታ ክራይ ከፍለን እንዴት እንችላለን?” ስሉ አንድ በነባሩ ክልል ሰራተኛ የነበረ ግለሰብ ከእንደገና ሲዋቀር ያመጣው ጉዳት በተመለከተ ገልፀውልናል።

ከመንግሥት ሰራተኞች እንግልት፣ ከህዝብ መንግታዊ አገልግሎት ለማግኘት ከቦታ ወደ ቦታ ግዜ፣ ገንዘብና ጉልበት አውጥቶ ከመንከራተት ጩሄት በተጨማሪ ሰሞኑን በተፈጠረው “ክልሉ እውን እንዲሆን በታገልነው ልክ ስልጣን አልተሰጠኝም” የሚሉ ግለሰቦች ውዝግብ ምክንያት ቆይተው የነበረው የዎላይታ ዞን እና የጋሞ ዞን ህዝቦች ምክርቤት በሹም ሽረት ምክንያት ከኃላፊነት የተነሱ ግለሰቦች ቦታ የየዞኑ አስተዳዳሪ እና ሌሎችን ለመሾም ጳጉሜ 02-03 (ጋሞ)፤ 03-04 (ዎላይታ) 2015 ዓ.ም ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *