በጋሞ ዞን ከጥንት ጀምሮ ስናከብር የመጣነው የራሳችን ዘመን መለወጫ እያለን ዮ ማስቃላ የተባለውን ለማክበር እየተገደድን ነው” የቁጫ እና የዘይሴ ብሄረሰቦች ቅሬታ

የዘይሴና የቁጫ ብሄረሰብ ተወካዮች በጋሞ ዞን ውስጥ ያለማንነታቸው ተገዶ ስለሚያከብሩት በዓል ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደሚከተለው አድርሷል።

“የዛይሴ ብሔረሰብ ላለፉት አስራ ስድስት ክፍለ ዘመናት ሉአላዊ ግዛቱን አስጠብቆ የኖረ ህዝብ ሲሆን በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት በ17ኛው ንጉስ ካት ካማ የአስተዳደር ዘመን ከከባድ ጦርነት በኋላ ወደ ማእከላዊ መንግስቱ የተጠቃለለ ግዛት ነው። ከሃያ በላይ ነገሥታት ተፈራርቀው ያስተዳደሩት ፣ ሃያ ስምንት ማጋዎቾ ያሉት፣ የታሪክ ሀብታም እና የቱባ ባህል ባለቤት የሆነ ኩሩ ህዝብ ነው።

ካሉት ባህላዊ እውቀትና እሴቶች መካከል አንዱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር ቆይቶ ዛሬ ላይ የደረሰው የዘመን ቀመር አንዱ ነው። በብሔረሰቡ የዘመን ቀመር መሰረት ዘመን መለወጫ በዓል የሚከበረው በ’ቢዛ አጉና ቆስ ቢዞ’ (ወርሀ ሰኔ ቀን አንድ) ሲሆን ይህም የዎ ሱሩቄ በመባል ይታወቃል።

ይህን የሚያረጋግጡ ህያው ማስረጃዎች ተሰብስበው የተለያዩ መጽሐፍት በመንግስት እውቅና አግኝተው ታትመዋል። ልጆችም ባህላቸውን አውቀው ያድጉ ዘንድ በተለያዩ ክፍሎች መማርያ መጽሐፍቶች ውስጥ ተካቶ እየተማሩ ይገኛል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በተለይ የጋሞ ዞን ሆን ብሎ ሐይማኖታዊ በዓል የሆነውን ቡዶ ኬሶ የዛይሴ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ አድርጎ ላማክበር ያደረገው ጥረት በእውነቱ ያሳዝናል።

የእስራኤል ህዝብ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ በዓለም ዙርያ ተበትኖ ነበር። ከብዙ ዘመን በኋላ በ19ኛው መቶ ክፋለ ዘመን ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው ከሁለተኛው የአዓለም ጦርነት በኋላ እስራኤልን ዳግም አጽንተዋል። የዚህ ሚስጥር አንድ ነው። በሄዱበት ሀገር ሁሉ ባህላቸውንና ማንነታቸውን ጠብቀው መኖራቸው ነው።

የዛይሴ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ሰኔ አንድ የሚከበረው የዎ ሱሩቄ እንደ ሆነ በትውልዱ ልብ ውስጥ ታትሟል። ከዚህ በላይ ስኬት የለም። ባህሉና ማንነቱ ነው። ማንም ሊነፍገው አይችልምና ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላም ቢሆን ያከብረዋል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ አህያ የጅብ ነው።

የዛይሴን ብሔረሰብ ባህል በመሸርሸር በጊዜ ሂደት ብሔረሰቡን ታሪክ አልባ ለማድረግ ጋሞ ዞን የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑን ህዝባችን ተረድቶ ከዚህ እኩይ አላማ እራሱን ነቅቶ ሊጠብቅ ይገባል።

በሌላ በኩል በቁጫዎች የሚከበረውና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የቁጫ ሕዝብ ዘመን መለወጫ በዓሉ ዎዳላ ጋዜ/Wodala Gazze/ ነው እንጂ ዮ ጋሞ ማስቃላ የሚባል አይደለም። ይህንን ከማንም በላይ የሚያውቀው የጋሞ ሕዝብ ነው። ምክንያቱም የጋሞ ሕዝብ የቁጫን ሕዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ እና ሌሎች ትውፊቶችን ከየትኛውም የጎረቤት ሕዝብ በላይ ያውቀዋል። የቁጫ ሕዝብም በዚያው ልክ የጋሞን ሕዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እና ሌሎች ትውፊቶችን በደንብ ያውቃል። የቁጫ ሕዝብ ሲያውቅ ጋሞ የሚባል ብሄረሰብ ካለ የጋሞ ሕዝብ ነው እንጂ የጋሞ ሕዝቦች የሚባል ነገር የለም።

በመጭረሻም ለመላው የቁጫ ሕዝብ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ላላችሁ ፈጣሪ እንኳን ለቁጫ ሕዝብ ዘመን መለወጫ በዓል ለሆነው ዎዳላ ጋዜ በዓል አደረሳችሁ፥ አደረሰንም እያልን ቅርስ ያለው ታሪክ አለው በሚል መርህ መሠረት የቁጫን ሕዝብ ታሪክና ባህል አካል የሆነውን ዎዳላ ጋዜ በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የበኩላችሁን እንድትወጡ አክብሮታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።" ሲሉ የዘይሴና የቁጫ ብሄረሰብ ተወካዮች በጋሞ ዞን ውስጥ ያለማንነታቸው ተገዶ ስለሚያከብሩት በዓል ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በጋራ በላኩት መረጃ አስረድቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: