

“የዎላይታ ህዝብ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ነፃነት የሚረጋገጠው በስጦታ ሳይሆን በብርቱ ትግል በሚመሰረተው ዎላይታ ብሄራዊ ክልል ነው” አቶ ጎዘቤ ጎኣ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “ለዎላይታ ህዝብ የፖለቲካ፣ የኢኮሚና የመልማት እድል ያስገኛል ብሎ የሚያስብ ዎላይታ የለም ካለም አንቀላፍተዋልና አንቁት” ሲሉ የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጎኣ በተለይም ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል።
የዎላይታ ህዝብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት የሚረጋገጠው በክንዱ በሚመሰርተው “በዎላይታ ብሄራዊ ክልል” ነው ያሉት ሊቀመንበሩ “ይህ የሚሆነው የፖለቲካ ቁማርና አጨዋወቱን በሚገባ በመረዳት በመጣበት መንገድ በማስተናገድ እንጂ ከመጣው ሁሉ ጋር ዳንኪራ በመጨፈር አይደለም” ሲሉ አውግዘዋል።
የዎህዴግ ሊቀመንበሩ አቶ ገበዜ ሁኔታውን ሲገልፁ “ይሄንን ስላችሁ እንዲሁ በቅናት ሳይሆን በእውቀትና በፖለቲካ ትንታኔ አሁን የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዎላይታ ህዝብ የዘመናት ጥያቄ የሆነውን “Wolaytta asaa kawotettaa oyshaa” የዎላይታ ብሄረ መንግስት ጥያቄ (ክልል) ለማጨናገፍና ባለቤት አልባ መዋቅር አድርጎ ለመፍጠር ታስቦ የተሰራ ሴራ ነው እንጂ የህዝቦች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ስብራቶችን ለመጠገን የተገነባ መዋቅር አለመሆኑን ዎላይታዊያን ልገነዘቡት ይገባል” ሲሉም አብራርተዋል።
“ህዝባችንን ከዚህ አደረጃጀት በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ እንዲሁም በሰለጠነ መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማላቀቅ የጀመርነውን ህዝባዊና ሰላማዊ ትግል በመደገፍ ከፖለቲካ ግዞታዊ እስር ቤት እንደህዝብ እንድንላቀቅ በታላቅ አክብሮት ላሳስባችሁ እወዳለሁ” ሲሉም ሊቀመንበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዎህዴግ እና ዎብን “ከህገመንግስቱ አሰራር ውጪ ስልጣናቸውን አለአግባብ በመጠቀም ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሱ ነው” ባሏቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ላይ በአዲስአበባ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ “የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነት” ችሎት ላይ “የዎላይታ ህዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በጣሱ ተከሳሾች ጋር እየተካሰሱ መሆኑ ይታወቃል።


የዎብን ሊቀመንበር ዶክተር አማኑኤል ሞግሶ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በወቅቱ እንደገለፁት “በተከሳሽ ወገን የቀረቡ ተቃውሞ ውድቅ ተደርጐ ሁለቱ ፓርቲዎቹ ያስገቡት የሰነድና የሰው ማስረጃ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቷል” ሲሉ መናገራቸውን ዘግበን እንደነበር ይታወሳል።
“ብልፅግና ፓርቲ መልስ ባለመስጠቱ እና ፍርድ ቤት ባለመቅረቡ ጠበቆቻችን ባቀረቡት የመከራከር መብታቸው ተነፍጎ በሌሉበት እንዲታይ ብለው ባቀረቡት ፍርድ ቤቱ ተቀብሎ በብልፅግና ፓርቲ በሌሉበት እንዲታይ ተወስኖበታል” ስሉም የፓርቲው ሊቀመንበሩ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተው ነበር።

ሊቀመንበሩ “ያቀረብነውን መረጃ ተመልክተው ተከሳሾች ባቀረቡት መልስ ላይ የመጀመሪያ ክስ ማሰማት ሂደት ለመግባት ተከሳሾች አሁን እንዳይሆን በመፈለጋቸውና በማስረጃው ተጨማሪ መልስ ሊያስፈልግ ይችላል” በማለታቸው ቀጣይ ክስ መቃወሚያ የሚሰማበት ለጥቅምት 2/2016 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀጠሮ መያዙን መዘገባችን ይታወቃል።