የመንግስታዊ መዋቅር ፍጥጫ የፈጠረው የወንድማማች ህዝቦች አንድነት የሚጠግን ማን ይሁን ❓

በተለይም በላፉት አምስት አመታት የቀድሞ ደቡብ ክልል አደራጃጀት ጥያቄ ተያይዘው በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ የተፈጠሩ ክስተቶች ለአጎራባች ህዝቦች ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አንድነት መሸርሸር፥ ለዘመናት በተለያዩ መንገዶች የተጋመዱ ህዝቦች ( ዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ዳውሮ፣ ሲዳማ… ወዘተ ) እርስበርሳቸው በጥርጣሬ እንዲመለከቱ በተወሰነ ደረጃም የራሱን አሉታዊ አስተውፅኦ አበርክቷል፥ እያበረከተም ይገኛል።

ከፓለቲካ ሴራ የፀዳ የህዝቦች እውነተኛ ህዝብ ለህዝብ አንድነት ለህብረተሰቡ ዕድገትና ልማት መሠረት ነው፥ መደማመጥና መተባበር ካለ ደግሞ የትኛውንም ተግባር በጋራ ተጋግዘን ለመውጣት መሰላል ይሆናል። አጎራባች ህዝቦች ይቅርና ከሩቅ የሚኖር ህዝብ እንኳን መደጋገፍ ካለ በሀሳብ ልዩነት ሆነን እየተከራከርን የምናጠፋውን ጊዜ ለልማት ተጠቅመን አከባቢያችንና ሀገራችንን ኢትዮጵያን በተገቢውና በተግባር ማገዝ እንችላለን።

አሁን ግን ለሕዘባችን ከዴሞክራሲም ከምንም በላይ ሰላም ያሰፈልገዋል፡፡ ልጆች ሰርተው ለመለውጥ ሕዛባችን ከችግር ለመላቀቅ ከፖለቲካ እሰጣገባ ወጥተን ሰላማችን ላይ ማተኮር ይኖርብናል፡፡ ሰላም በቤታችን፤ ከጎረበቶቻችን ጋር ያሰፈልገናል፡፡ ያለፉትን 5 ዓመታት ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ ሆኖ ማንም በስራ ሳይፈተን ህዝቡ በችግር እያሳለፈ ነው፡፡ ይሄ ሁኔታ ልቆም ይገባል፡፡ ያንን ለማድረግ የሚያለያዩንን ነገር ከማስፋት ይልቅ በሚያቀራርቡ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ለህዘባችን ቅድሚያ ሰላሙን መሸመት ያሰፈልገናል።

በመሆኑም በተለይም በዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ዳውሮ፣ ሲዳማ እንዲሁም በዙሪያው የምትገኙ ምሁራን፣ ፓለቲከኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም በየደረጃው ተሰምነት ያላችሁ ታላላቆች፦ ባለፉት አምስት አመታት በአከባቢው ፓለቲካ አካሄድ ልዩነት ምክንያት ብቻ ዳርና ዳር ሆነው የሚገኙ ወገኖች እንዲሁም በፓለቲካ ቁርሾ ምክንያት የተፈጠረ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደ አንድነት፣ መደማመጥ፣ መተባበር እንዲሁም በጋራ ጉዳይ በሆኑ የህዝብ የልማት ፍላጎቶች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡና በአንድነት በመሰለፍ በጎ ሚና ሊወጡ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የምክክር መድረክ ቢዘጋጅ ለህብረተሰቡ ዘላቂና ጠቃሚ ዕድሎችን ይዘው ይመጣል።

ባለፉት አምስት አመታት መቀራረብና መደማመጥ በተገቢው በህዝቦች መካከል ስላልነበረ ቢተጋገዙ ታአምር ሊፈጥር የሚችል የሰውና የተፈጥሮ ሀብት ቢኖርም ሁሉም በተናጠል በመጓዛቸው በአንድነት ለማሰለፍ የሚተጋ ባለራዕይ መሪና ተቋም ባለመኖሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙት የሚሰጠውን ፀጋ ማጣት ብቻ ሳይሆን በአከባቢው ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

የአጎራባች ህዝቦች የሀሳብና በየጊዜው የሚቀያየር የፓለቲካ አካሄድ ልዩነት በጋራ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ የጋራ መድረክ ፈጥሮ ከመስራት ፈፅሞ ሊያራርቀን አይገባም። ይሄ ዕቅድ እውን እንዲሆን ሁላችንም ያለፈው ቁርሾ ላይ ትኩረት ማድረግን ትተን ከፊታችን ባለው ከህዝብ ለህዝብ ግንኘነት በሚገኘው መልካም ዕድልና ምቹ አጋጣሚ ለህብረተሰቡ ለማምጣት የበኩላችንን ከልብ ለማበርከት በያለንበት ዝግጁ መሆን አለብን እያልን ልዩነቱ በውይይትና በመግባባት የሚፈታበት ሁኔታ ቢመቻች ሁልጊዜ በዚህ ልዩነት ምክንያት በሚከሰቱ ጦርነቶች የሚሞቱ ንፁሃንና የሚወድም የሀገር ሀብት ተርፎ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት በር ከፋች ይሆናል ብለን እናስባለን🤲

ይሄ ከፓለቲካ ባሻገር የአጎራባች ህዝቦች እርስበርስ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የታለመው ሀሳብ ወደ መሬት እንዲወርድ የሚያግዙ መጋቢ ሀሳቦችን ለህብረተሰቡ በማቅረብ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከትም ዝግጁ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

ሰላም ለሀገራችን 🇪🇹🤲

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *