የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲታወሱ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከመሆናቸው በፊት ከዩኒቨርስቲ መምህርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ከአንዱ ወደሌላኛው ኃላፊነት ባላቸው በስራ ልምድና ክህሎት እንዲሁም ፍፁም ሌብነትን በመፀየፍ በማገልገል እየተሸጋገሩ አሁንም በተለያዩ አለምአቀፋዊ ተቋማት የአመራርነት ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድንገት ወይንም በአጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ የሚመስላቸዉ፣ አንዳንድ በብሄረተኝነት ተውጠው ኢትዮጵያዊነት ሲያሳድግ (ሲቀርጽ) የበደላቸዉ የዋህ ወገኖቻችንና የሐገሪቱን ችግሮች በባዶ አዕምሮአቸዉ ተሸክመዉ እነሆ መፍትሔ እያሉ ችግር ላይ ችግር የሚደርቡ የተወሰነ ጭብጥ እንዲያገኙ ይህቺ በአጭሩ የታሪክ ዳራ የዳሰሰች ፅሁፍ አስፈልጓል።

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ከማንሳታችን በፊት እርሳቸዉን ያፈራዉን ብሄር ዎላይታን ፖለቲካዊ ታሪክ ከእርሳቸዉ የሁዋላ ታሪክ ጋር በጥቂቱ መዳሰስ ያስፈልጋል። የዎላይታ ሕዝብ የኢትዮጵያ ኢምፓየር አካል የሆነዉ፣ ከአስደናቂ የሰባት ዓመት ትንቅንቅና ተጋድሎ በሁዋላ ሐገሩ ፈርሶበት መሆኑ መሠመር አለበት።

በአፀ ሚኒሊክ መሪነት ከሚመራዉ የኢትዮጵያ ጦርና በንጉስ ጦና በሚመራዉ የዎላይታ ጦር መሐከል ከተካሄዱ ሰባት አሰቃቂ ጦርነቶች ስድስቱ ላይ ጦናና ሕዝባዊ ጦሩ፣ በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ሐገርነቱን አስጠብቆ መቆየቱ በታሪክ ይታወቃል። ከሰባተኛዉ ወረራና ጭፍጨፋ ማለፍ ባይችልም።

እንግዲህ በዚህ መንገድ ወደ ኢምፓየሩ የተቀላቀለዉ ሕዝብ ከአዉዳሚ የሰባት ዓመት ጦርነት በሁዋላ፣ የጠበቀዉ ከጦርነቱ ጠባሳ ሊያገግም ይቅርና ጦርነቱ የቀጠለ የሚመስል ሁኔታ ነበርና። ለዛም ይመስላል ከምርኮ መልስ በተሰጠዉ ስልጣን ተጠቅሞ ራሱ ንጉስ ጦና መልሶ ያመጸዉ፣ ብዙ ባይሳካለትም።

በአድዋ ጦርነት ወቅት ከዎላይታ የዘመተዉን ጦር ከመሩት ጦር መሪዎች አንዱ ነው የሚባለዉ ሐጤሮ ሐንቼ ከብዙ ትልልቅ የዎላይታ ሰዎች ጋር በድጋሚ ሌላ አመጽ ካቀነባበረ በሁዋላ፣ አመጹ የታቀደበት ቀን ሳይደርስ በአጋጣሚ ብቻዉን በወሰደዉ እርምጃ ብዙ ዉጤት ሳያመጣ ከሽፎበት በአሰቃቂ ሁኔታ ለመሞት የተገደደዉ። እንደዉም ፊታውራሪ ገነሜ የተባለ በሚኒሊክ ዎላይታን እንዲገዛ የተሾመ ሰው ወደ ሰገሌ ጦርነት መሄዱን ተከትሎ ሕዝቡ አመጽ በመቀስቀሱ ከፍተኛ ቅጣት ደርሶበታል።

የዎላይታ ሕዝብ ልጅ ኢያሱ ስልጣን ከሚኒሊክ ሲረከብ ጭቆና በዝቶብናልና መጥተህ ጎብኘን ብሎ መልዕክተኛ የላከና መልዕክቱም ተቀባይነት ያገኘለት ሕዝብ ነው፣ ጉብኝቱ ባይሳካም።

እናም ይህን ለመብቱና ለነጻነቱ ካለዉ ቀናኢነት የተነሳ ለበዝባዥ ሥርዓቶች የማይመቸዉን ሕዝብ ከመአከል ርቆ እንዲያስተዳድር የተወሰነበትና በአሜሪካ ሐገር ትምህርት ተከታትሎ የመጣዉ ተራማጁ ገርማሜ ነዋይ በዎላይታም ሆነ በኢትዮጵያ የለኮሰዉን የለዉጥ ችቦ የምንቃኝ ይሆናል።

ገርማሜ ነዋይን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ምን ያገናኘዋል❓

ተራማጁ ምሁር ገርማሜ ነዋይ የዎላይታ አዉራጃ አስተዳዳሪ ተደርጎ በአጼ ኃይለስላሴ መመደቡ በግፈኛ አገዛዝ ለሚማቅቀዉ የዎላይታ ሕዝብ መልካም እድል ነበረ። ገርማሜ በዎላይታ አዉራጃ ለዉጥ ለማምጣት ከግፈኛ መልከኞች ጋር የሚያደርገዉ ትንቅንቅ በንጉሱ አልተወደደምና ወደ ሌላኛዉ የባሰ ጠረፍ ኦጋዴን እንዲመደብ የተደረገ ቢሆንም እሱ ከዎላይታ ልጆች ጋር የማይበጠስ ትስስር ፈጥሮ ነበርና ለለዉጥ ሕልሙ ተግባራዊነት እሳት ፊት መቆም ሲኖርበት እርዳታቸዉ አስፈልጎታል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሪ የነበሩ ወቅት ለበዓል ከባለቤታቸው ጋር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጋብዘዉ በነበራቸዉ ቆይታ እንደሚከተለዉ ይላሉ የአባታቸዉን ታሪክ ሲያወሩ “አባቴ በትምህርት በጣም በጣም ጎቦዝ ነበር። በነሱ ጊዜ በዎላይታ አካባቢ እስከስምንተኛ ክፍል ብቻ ነበር ትምህርት የነበረዉ። እና ተፈሪ መኮንን ነው እስከ አስራ አንደኛ የተማረዉ።

የ53ቱ የነገርማሜ ብጥብጥ ተሳታፊ ስለነበረ ነው ትምህርቱን አቋዋርጦ ገጠር የገባዉ። አባቴ ሸሽቶ ነው ገጠር የገባዉ፣ ትምህርቱን አልጨረሰም። ሸሽቶ ገጠር ገብቶ …ገርማሜ ነዋይ የዎላይታ አዉራጃ አስተዳዳሪ ነበር እና ከእነዚህ ከዎላይታ ከመጡ ሐይስኩል ከሚማሩ ጋር ኔትዎርክ ፈጥሮ ነበር። ይሄ ነገር ሲነቃና የእነ ገርማሜው ሲከሽፍ አባቴና ጓዋደኞቹ መሸሽ ነበረባቸዉ። ሸሽቶ ገበሬ መስሎ ገጠር ገባ። “ኃይለማሪያም ደሳለኝ

በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ የተሳተፉና ያመለጡ የዎላይታ ተማሪዎች ጉዳይ አንደኛ ጀግንነት ሲሆን ፣ ሁለተኛ በወቅቱ ስዩመ እግዚአብሔር ነኝ የሚለዉን አስከፊ ንጉሳዊ ሥርዓት ለመገርሰስ ከተራማጅ ኃይሎች ጋር ተሰልፎ መንቀሳቀስ ቀድሞ መንቃትን ያመለክታል።

በወቅቱ በቁጥጥር ስር ዉሎ ተገድዶ በረዲዮ ለሕዝብ መልዕክት ያስተላለፈዉ ልዑል አልጋ ወራሸ አስፋወሰን እንደሚከተለዉ ብሎ ነበር ፣ ለተማሩ ወጣቶች ተሳትፎም ጭምር እዉቅና የሚሰጥ ንግግር ያቀረበዉ“ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ3000 አመታት በላይ የሚታወቅ ታሪክ አለው።

ነገር ግን በዚህ ጊዜ ውስጥ ገበሬዉ ከሞፈር ከደግርና ከቀንበር የእርሻ መሳሪያ፣ ነጋዴዉ ከችርቻሮ ሌላዉ በልዩ ልዩ የሚተዳደር አባቶች ካቆዩት ያአሰራር ዘዴ ያልወጣ ነዉ። በጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከድንቁር የኑሮ ደረጃ እስከ ዛሬ ሊወጣ አልቻለም፡፡

የአስተዳደር አመራር ዓላማም ሕግንና ሥርዓትን መሰረት አድርጎ ህዝብን መበደያና መጨቆኛ አይነተኝ መሳሪያ ሆኖ ቀረ…………” እያሉ የስርዓቱን አስከፊነት እና የለውጥ አስፈላጊነትን አስረግጠዉ ተናገሩ፡፡ አያይዘውም እንዲ ሲሉ ሰለ ራሳቸዉ አዲስ በተቋቋመዉ መንግስት ውስጥ እንዴት ህዝቡን ሊያገለግሉ እንደተዘጋጁ ተናዘዙ “…. ከዛሬ ጀምሮ በሃብት በኩል እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሆኜ በሚቆረጥልኝ ደሞዝ ብቻ በስልጣኔ እዉነተኛዉን ህገ መንግስት መመሪያ በማድረግ ሀገሬና የኢትዮጵያ ህዝብ ፍጹም በሆነ ቅን ልቦና ለመስራት ወስኛለሁ።

….አዲስ የተቋቋመዉ የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስት በኔው በራሴ፣ በጦር ክፍሎቸ፣ በፖሊስ ሰራዊት፣ በተማሩ ወጣቶችና እንዲሁም በኢትዮጵያ ህዝብ የተደገፈ በመሆኑ የሚደረገዉ ሹም ሽርም ሆነ ስራው ማንኛውም ዓይነት ውሳኔ የጸና ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በዓለም ህዝብ ፊት ተገቢ የሆነውን ግርማ ሞገስ የተጎናጸፈ ክብር የሚያስገኝልህ ታሪክ መሆኑን አውቀህ ኅብረትህ ከብረት የጠነከረ ይሁን።” ሌላኛው ክፍል ይቀጥላል..

በፕሮፌሰር ዎላይታ ይመጣል (የብዕር ስም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: