ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ ከተደራጀ ወዲህ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያወጣ ቢሆንም የመንግስት ሰራተኞች ደመውዝ አለመክፈሉ ተነገረ።

ከልዩ ወረዳነት ወደ ዞንነት የተዋቀሩ አምስት የዞን መዋቅሮችን ጨምሮ አስር ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በአንድነት የመሰረቱት “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ክልል መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተለያዩ ቦታዎች ጀምሯል ቢባልም ከተወሰኑት ውጪ አብዛኞቹ አለመጀመራቸው በህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ እያስተናገደ መሆኑም ተገልጿል።

አንድ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደገለፀው “አዲሱ ክልል ከተመሰረተ ጀምሮ በአበል፣ በመስተንግዶ እና የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት እየተባለ በርካታ ገንዘብ ከመንግሥት ካዝና ወጪ እየተደረገ ነው” ስል አብራርተዋል።

ክልሉ ከተመሰረተ ሁለት ወር ሳይሞላ በአበል፣ በመስተንግዶና የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት ተብሎ 3.5 ቢሊዮን ብር፣ ለነዳጅና ናፍጣ 4.2 ቢሊዮን ብር በሰነድ ወጪ መደረጉን ከፍተኛ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ባለሙያ አክለው አስረድተዋል።

በተቃራኒው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአዲስ መልክ ክልሉ ከተደራጀ ጀምሮ በቅርቡ ከተከፈለው የመምህራን ደመወዝ ወጪ ለሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ደመውዝ አለመክፈሉ በሰራተኞች መካከል ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠረ ስለመሆኑ አንድ በክልሉ ቢሮ የሚሰራ ግለሰብ አብራርተዋል።

በክልሉ የክልል መዋቅር ብቻ ሳይሆን የዞንና የወረዳ መዋቅር የሚሰሩ የመንግስት ሰራተኞቹም ደምወዝ እንዳልተከፈላቸው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል ክልሉ “መንግስታዊ አገልግሎቶችን መስጠት በተለያዩ ቦታዎች ጀምሯል” ቢባልም ከተወሰኑት ውጪ አብዛኞቹ አለመጀመራቸውና የቀድሞ ደቡብ ክልል ሲፈርስ ወደ አዲሱ ክልል መዋቅር እንዲሄዱ የተመደቡ መንግስት ሰራተኞችም ወደ ተመደቡበት ቦታ አለመሄዳቸው በህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ እያስተናገደ ለጊዜ፣ ለገንዘብ እንዲሁም ለመልካም አስተዳደር ችግሮች መነሻ እየሆነ መሆኑም ተነግሯል። Wolaita Times

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: