በጋዜጠኞችና በብዙኃን መገናኛ ተቋማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት ሕጋዊ ሥርዓትን ብቻ የተከተለ ሊሆን ይገባል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠይቋል።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ላይ ከሕግ አካሄድ ውጪ አሥሮ የማቆየትና ለስርጭት የተዘጋጀ የህትመት ውጤትን የማገድ ድርጊቶች እንደተፈፀመባቸውና በዚህም ሳቢያ ተቋማቱ የእለት ተዕለት ስራዎቻቸውን ለመስራት መቸገራቸውን አስታውቋል (የዎላይታ ታይምስ ሚዲያም በዚህ ምክንያት ወደ ሌላ ሀገር በመሰደድ ለመስራት መገደዱ ይታወቃል)።

ላለፉት አምስት ዓመታት የፍትህ አካሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም ጋዜጠኞችንና ተቋማቱን በተመለከተ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ ምክር ቤቱን በእጅጉ እንዳሳሰበው የገለፀው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ችግሩ እንዲፈታ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ጉዳዩን በማሳወቅ ክትትል እያደረገ መሆኑን በመግለጫው ጠቅሷል።

ጽንፈኝነት የሀገሪቱን አየር በተቆጣጠረበት ሁኔታ ሙያውን የሚያውቁ ሚዛናዊነትን ሊጠብቁ የሚሞክሩ ይገፋሉ ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ የገለጸው ቴዎድሮስ ገበያው እራሱ የሚፈልጋቸው አይሆንም ስለሆነም በዚህ ምክንያት ከሙያው ይገለላሉ ብሏል።

ለእነዚህ ነገሮች በሙሉ ሀላፊነት መውሰድ ያለበት መንግስት መሆኑን የጠቆመን ቴዎድሮስ አስፋው “ጽንፈኝነት በዚህ ደረጃ የፖለቲካው መገለጫ ሲሆን ሁላችንም የህልውና አይነት ትግል ውስጥ የምንገባ ከሆነ፤ በእንደዚህ አይነት ወቅት ላይ ሙያተኛ ሁን ማለት እንደቅንጦት የሚታይ ይመስለኛል፤ ይህንን ማርገብ፣ አቻቻይ የሆነ ሚዛናዊ የሆኑ ዘገባዎችን ለመስራት፣ ትንታኔዎችን ለመስጠት የሚረዳ ይመስለኛል” ሲል አካፍሎናል።

ስለዚህ ሁሉም የእኔ ነው የሚለውን አካል ከህልውና ለማትረፍ፣ ከተሸናፊነት ለማትረፍ፤ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ፍላጎቱን እንዲሟላለት ለማድረግ ሙያውን ጭምር አላስፈላጊ ቢሆንም ተገቢ ባልሆነ ሙያዊ ባልሆነ መንገድ ለመጠቀም እስከመገደድ ይደርሳል ማለት መሆኑን አመላክቷል።

የሀገሪቱ የጋዜጠኝነት ሞያ ዋነኛ ችግር ሞያው የተሞላው ሞያውን በማያውቁት ሰዎች መሆኑ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ለአዲስ ስታንዳርደ አስተያየቱን አጋርቷል። 

 የእኛ ሀገር የጋዜጠኝነት ሞያ ከመጀመሪያውም ጀምሮ በብዙ ችግሮች ውስጥ ያለና የመጣ ነው ሲል የነገረን ጥበቡ በለጠ በሀገሪቱ ሙያው በባለሞያተኞች የተያዘ እንዳይደለ እና ትኩረት እንዳልተሰጠው ግልጽ ማሳያ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ነጻ መገናኛ ብዙሃን እና የኢትዮጵያ የግል ባንኮች በእኩል ዘመን ወደ ስራ መግባታቸውን ያወሳው የማህበሩ ፕሬዝዳንት ነገር ግን ዛሬ ባንኮቹ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ገንብተው ቢዝነሶችን የሚያንቀሳቅሱ የኢኮነሚው አውታር ሆነዋል፣ መገናኛ ብዙሃኑ ደግሞ ከምድር ላይ የመጥፋት ሁኔታ ነው የሚታይባቸው ሲል በንጽጽር አቅርቧል።

ይህ የአየያዝ ጉዳይ ነው ያለን ጥበቡ ባንኮችን መንግስተ ስለሚደግፋቸው፣ ስለሚቆጣጠራቸው እንዲያድጉ እንዲበለጽጉ ብዙ ነገር ስለሚደረግላቸው አደጉ፤ መገናኛ ብዙሃኑ ስለሚኮረኮሙ እና ብዙ ጫና ስላለባቸው ተዳክመው ሞቱ ማለት ይቻላል ብሎናል።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ወደ መዝናኛው ዘርፍ እያተኮሩ ይገኛሉ ለምን?

የህዝብ አጀንዳ የሚያቀነቅኑ የግል መገናኛ ብዙሃን እየከሰሙ ይገኛሉ፣ በአንጻሩ መዝናኛ ላይ የሚያተኩሩ በርካታ የሬድዮ እና የኢንተርኔት ዘርፎች ደግሞ ፈልተዋል፡፡ ይህ ወቅት ወሳኝ የሆኑት ጉዳዮች ለህዝቡ ሊደርሱ የሚገባበት ወቅት ነው። ምሁራንና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሊከራከሩበት፣ ሀሳብ ሊንሸራሸርበት፣ ውይይቶች ሊደረጉበት የሚሻ ወቅት ነው። ነገር ግን ይህ ሁሉ በሀገሪቱ አይታይም።

በትግራይ ላይ ጦትነት በተካሄደበት ወቅት ሚዲያዎቹ ለምንድን ነው ይሄ ጦርነት የሚካሄደው ከማለት ይልቅ የመንግስት መሳሪያ ነበሩ። የጦርነቱ መሳሪያ ነበሩ። አብዘሃኛዎቹ የመዝናኛ ዘገባዎቻቸውን ትተው ሁሉ ሙሉ አጀንዳቸውን ቅስቀሳ ላይ የጦርነቱ ውሎዎች ላይ ትኩረት ያረጉበት ግዜ ነበር። ሚዲያው የሀገር ውስጥ ጦርነት እንጂ ከውጭ ጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነት አለመሆኑን የሚያጠይቅ ፕላትፎርሙን መፍጠር ነበረበት። ግን አላደረገም። 

በሀገር ውስጥ ተመዝግበው ከሚሰራጩ መገናኛ ብዙሃን ችግር ሳይደርስባቸው የነጻነት አየር በመተንፈስ ላይ ያሉት በመዝናኛው ዘርፍ የተሰማሩት ብቻ ይመስላል። በሀገሪቱ በተለይም በዋና ከተማዋ ያሉ የአጭር ስርጭት ሬድዮ ጣቢያዎችም ሆነ፣ ተመዝግበው፣ ፍቃድ አግኝተው በኢንተርኔት የሚተላለፉ መገናኛ ብዙሃኑ ትኩረታቸው መዝናኛው ላይ ከሆነ ሰነባብቷል።

ለምን ስንል ጠየቅን፤ የመቀለ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን መምህሩ ማቴዎስ ገብረሂዎት አስተያየት “ሽሽት ነው” ሲሉ ምላሻቸውን የሰጡን ሲሆን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ጥበቡ በለጠ በበኩሉ “አያስጠይቅማ” ብሎናል።

መምህር ማቴዎስ ገብረሂዎት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን መዝናኛ ላይ እንዲያተኩሩ ያደረጋቸው ሽሽት እና ፍራቻ ዋናው ገፊው ምክንያት ነው ሲሉ ገልጸው በመዝናኛው ዘርፍ እራሱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ከማንሳት ይልቅ የውጭ ሀገራት የመዝናኛ ጉዳዮችን እንደሚያበዙ ተናግረዋል።

ፖለቲካ የሚፈራበት አትሞስፌር ስለተፈጠር ወደ መዝናኛው ፊታቸው መዞሩን አመላክተዋል። ጥበቡ በለጠ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት በበኩላቸው የመዝናኛ ዘገባዎች ስለማያስጠይቁ እና ወደ ፍራቻ ቆፈን ውስጥ ስለማያስገባ ነው ሲሉ ገልጸው ትኩረቱ በአውሮፓ እግር ኳስ እና መዝናኛ ላይ መሆኑ ህዝብን በተለይም ወጣቱን ለማደንዘዝ ብቻ ነው የሚጠቅመው ሲሉ ትዝብታቸውነ አካፍለውናል።

ታላላቅ የሀገሪቱ ድርጅቶች እና ተቋማት ገንዘባቸውን አፍስሰው ህዝቡን የሚያደነዝዙ ሁነቶችን ስፖንሰር እንደሚያደርጉ በመግለጽ ተችተዋል።

መታወቅ ያለበት ይላሉ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ መገናኛ ብዙሃኑ በተለይም የሀገራችን ሬድዮና እና ቴሌቪዥኖች መዝናኛ አይደለም የሚቀርበው፤ መዝናኛ ሌላ ዘውግ ነው ሲሉ ገልጸው የኛዎቹ የሚያቀርቡት የመዝናኛ ዘገባ ሳይሆን የማደንዘዣ ዘገባ ነው ሲሉ አሳስበዋል። 

መዝናኛ ሙያ ነው፣ ሙያተኛም ይፈልጋል፤ በመዝናኛ ውስጥ ሰውን ማሳወቅ፣ ሰውን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሳደግ፣ አዕምሮአዊ ብቃት እንዲኖረው ማድረግ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ነው። እያዝናናህ የምታስተምርበት ነው እንጂ የምታደነዝዝበት አይደለም። እኛ ጋ ወደ ማደንዘዣነት ነው የተቀየረው ይህ ያሳዝናል ብሏል።

በስደት የሚገኘው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው በበኩሉ አሁን ላይ ሀገር ውስጥ ያለው ሚዲያ እንዴት ነው ፖለቲካ ሊሰራ የሚችለው ሲል በመጠየቅ ሀገር ውስጥ ያለው ሚዲያ ፖለቲካ መስራት ስለማይችል እና ችግር ስለሚገጥመው ተገዶ ነው ወደ መዝናኛው የገባው ብሎናል። ፖለቲካ ላይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎች በሙሉ ከሀገር ውጭ ያሉ ናቸው ሲል ትዝብቱን አካፍሎናል። የዜና ምንጮች አስ፣ ዶቼቬሌ እና መገናኛ ብዙሃን ማህበር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: