የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ፀጋዬ ቱኬ በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” በቁጥጥር ስር ዋሉ።

አቶ ጸጋዬ በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የተያዙት፤ ለተወሰኑ ጊዜያት “ተሰውረው ከቆዩበት” አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ነው ተብሏል።

አቶ ጸጋዬ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 13፤ 2016 ረፋድ አምስት ሰዓት ገደማ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመያዛቸውን የሲዳማ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እያሱ ዳዊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

የቀድሞው ከንቲባ ለሶስት ዓመት ገደማ በኃላፊነት ሲያስተዳድሯት ወደቆዩት ሀዋሳ ከተማ፤ በሲዳማ ክልል እና በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ታጅበው ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ገደማ መድረሳቸውንም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ አቶ ጸጋዬ በሀዋሳ ከተማ ወደ “የእስረኛ ማቆያ” መወሰዳቸውን አስታውቋል።

የሲዳማ ክልል የጸጥታ ግብረ ኃይል፤ የቀድሞውን ከንቲባን በቁጥጥር ስር ለማዋል “ያልተቋረጠ ክትትል ሲያደርግ እንደነበርም” ቢሮው በመግለጫው ጠቁሟል።

አቶ ጸጋዬ በክልል ደረጃ ሲካሄድ የነበረን “የአመራር ግምገማ ረግጠው በመውጣት ተሸሽገው እንደነበር” የጠቀሰው የቢሮው መግለጫ፤ ይህንን ያደረጉትም “ከተጠረጠሩበት ወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ” እንደሆነ አመልክቷል።

የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ ባለፈው ነሐሴ ወር በተካሄደ የክልሉ መንግስት እና ገዢ ፓርቲ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” መገምገማቸው የኢትዮጵያ እንሳይደር ዘገባዎች ያመለክታል። Wolaita Times

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: