በዎላይታ ሶዶ ከተማ የተደራጀ የከተማ መሬት ዝርፊያ መጧጧፉ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን የምርምር ዘገባ አመላከተ

መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በማህበር ተደራጅተው መሬትን በምደባ የሚሰጥበት መልካም አሠራር ዘርግቶ ነበር። ይህንን ምቹ አጋጣሚን በመጠቀም በዎላይታ ሶዶ ከተማ አንዳንድ የዞን እና የከተማ አመራሮች በሞቱ ሰዎች ስም፣ በቤት ሠራተኞቻቸው ስም፣ በገጠር ወረዳ በሚገኙ አርሶአደር ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ስም፣ በጎዳና ተዳዳሪዎች ስም፣ ወዘተ ከ412 (አራት መቶ አሥራ ሁለት) በላይ ሕገወጥ ( Ghost ) ማህበራትን በማደራጀት፣ የተጨብረበረ ሐሰተኛ የባንክ ስሊፕ በማቅረብ፣ የተደራጁበትን ቀን ወደኋላ በመጻፍ ( Backdate በማድረግ )፣ ወዘተ ውድና ውስን የሕዝብ ሀብት የሆነውን የከተማ መሬትን እየመዘበሩ እንደሚገኙ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በተለያዩ መንገዶች ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥልቅ ምርመራ አረጋግጧል።

ይህንን ሕገወጥ ተግባርን በመፈጸምና በማስተባበር ግንባር ቀደም ተወናይ የሆኑት “አቶ አሥራት አየለ የቀድሞ የከተማ አስተዳደሩ ጽ/ቤት ኃላፊና የአሁኑ የገቢዎች ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ወራና የከተማው ማዘጋጃ ቤት ም/ኃላፊና የቤቶች ዘርፍ ኃላፊና የአሁኑ የወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ በለጠ ጌጡ የከተማው ሕብረት ሥራ ኃላፊ፣ አቶ ጋርማሞ በከተማው የሕብረት ሥራ ባለሙያ፣ አቶ አበራ አሉላ የዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራር፣ አቶ ምህረቱ ዳና የዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አመራርና የወጣቶች ፌዴሬሸን ፕረዝዳንት”.. ወዘተ እንደሚጠቀሱ ባደረግነው ጥብቅ ምርመራ ዘገባ በተጨባጭ መረጃ አረጋግጠን ፍርድቤት ያላረጋገጠውን ግለሰቦች ስም ለጊዜው በይፋ መጥቀስ አግባብ ባይሆንም ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንፃር ለህብረተሰቡ ይፋ ለማድረግ ተገደናል።

ከአንድ እስከ አምስት ብሎክ አንድ ሰው ብቻውን አግኝቶ ለግል ባለሀብቶች እየቸበቸቡ ይገኛሉ። ከዚህም በተጨማሪ የማህበር አባል መተካካት በሚል አንድ ግለሰብ እስከ አሥር ማህበር ውስጥ እየተደራጀ መሬቷን ካገኘ በኃላ እስከ 50,000 ብር ኮሚሽን እየተወሰደ ስለመሆኑም ለማረጋገጥ ችለናል።

አንዳንድ የዞን አመራሮች ለሕገወጥ የከተማ ባለሙያዎች፣ አመራሮችና ነጋዴዎች ሽፋን በመስጠትና በመደለል በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ ሁኔታ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ አንድ የዎላይታ ሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት መሬት አስተዳደር ባለሙያ ገልጸዋል።

ከ412 በላይ ሕገወጥ ማህበራት መካከል የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ለአብነት፦ ባሎታ ማህበር፣ ዮቶሬ ማህበር፣ ዳናሳ ማህበር፣ ማርንዶስ ማህበር፣ ፕላኔት ማህበር፣ – – – ወዘተ የዞንና የከተማ ቁልፍ አመራሮች ጎስት (ፎርጅድ) ማህበራት እንደሆኑም ስሙ እንዳይጠቀስ የገለጸው ባለሙያ ጠቁመዋል።

ነገር ግን በሕጋዊ አካሄድ በማህበር ተደራጅተው ሁሉንም ተፈላጊ መስፈርቶችን ያሟሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ መምህራን፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ተፈናቃዮች፣ ወዘተ ከአንድ ዓመት በላይ እየተንከራተቱና እየተጉላሉ የአመራር ድጋፍ ላላቸው ለእነዚህ ሕገወጥ ማህበራት በሣምንታት ውስጥ መሬት እንደሚሰጣቸው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ልዩ የምርምር ዘገባ አረጋግጧል።

በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከላይ የተጠቀሰውን ጉዳይ በአፋጣኝ በማጣራት እገዳ እንዲሰጥና ህጋዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን አፋጣኝ እርምጃ እንድትወስዱ እያሳሰብን ይህንን የማታደርጉ ከሆነ ለጊዜው ሙሉ ሰነድ ይፋ ካደረግን የፍርድና ህጋዊ ሂደት ሊያዛባ ይችላል በሚል ያቆየነውን የሁሉንም ማህበራት እና አመራሮች በሰነድ የተደገፈ ሙሉ መረጃን ለሕዝብ ይፋ እንደምናደርግ አጥብቀን እናሳውቃለን።

የዎላይታ ሶዶ ከተማ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እንዲሁም ለኑሮ ምቹ የሆነች፣ ባለሰባት መግቢያ በሮች ባለቤት በመሆን በየጊዜው በምታሳየው ከፍተኛ ዘርፈብዙ ዕድገት ምክንያት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተመራጭ ከተማ እየሆነች ያለች በራሷ ገቢ የምትዳደር ሲሆን በቅርቡ የቀድሞ ደቡብ ክልል መፍረሱን ተከትሎ ደቡብ ኢትዮጵያ ተብሎ ለተቋቋመው አዲሱ ክልል የአስተዳደርና የፓለቲካ ማዕከል በመሆን በይፋ ምስረታ ተደርጎ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: