የዎላይታ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ከተቀላቀለ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት ለአንድ አላማ የቆመውን የበተነው ማነው ❓

ሁሉም ነገር ለጊዜው መስመር ባይዝም ከተልዕኮው ውጪ የዩኒቨርስቲውን ስልጣንና ሀብት በመጠቀም ለህብረተሰቡ የመፍትሄ አቅጣጫ ጠቋሚ መሆን ሲገባቸው በአከባቢውን ፓለቲካ ውስጥ ጠልቃ በመግባት ድብቅ ፍላጎታቸውን በማራመድ መዝረፍና ማዘረፍ፣ በአከባቢው መንግስት ትኩረት እንዳያደርግ የማይሰራ የውሸት ፕሮጀክቶች ይሰራሉ የሚል የማዘናጋት ወሬ በማባዛት፣ የሀሳብ ልየነት ያላቸው የለውጥ ኃይል በማሰርና በማሳሰር እንዲሁም ከስራና ከኃላፍነት ተባርረው እንዲሰቃዩ በማድረግ የተሰማሩ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ከፍተኛ አመራሮች ከስልጣን ተወግደው የህግ ተጠያቂነት እንዲኖር የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጨምሮ ሌሎች የአከባቢው የለውጥ ናፋቂዎች እና የውስጥ አርበኞች ባደረጉት የሞት ሽረት ትግል ጉዳዩ የሀገር አጀንዳ እስከመሆን ደርሶ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። ምንም እንኳን ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሰዎች ቦታ የሚተኩ ግለሰቦች አካሄድና ተያያዥ ብርቱ ትግል የሚጠይቅ የቤት ስራ ከፊት ቢኖርም።

ሌላው ከዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ በተጨማሪ የዎላይታ ዞን መንግስታዊ መዋቅር ከሌሎች አከባቢዎች በብዙ መንገድ የሚለይ ነገር አለው። ስልጣን በትውውቅ፣ በዝምድና እንዲሁም በጥቅማጥቅም ትስስር የተመሠረተ በመሆኑ በአከባቢው ዘመድ የለለው ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት የማይችልበት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ እያለ የአመራር ዘመድ ያለው ያለውድድር ወረቀት በግዢ ያመጣ የሚቀጠርበት፣ ጉቦና ብልሹ አሰራር የተለመደ አሰራር እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

በተጠቀሱ ጉዳዮች ዙሪያ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ በመረጃ የተደገፉ ተጨባጭ መረጃዎችን ለእናንተ ስናደርስ እንደነበር ይታወቃል። አሁን አሁን እንደዛ አይነት መንግስታዊ ስልጣን በመያዝ ህገወጥ የግልና የቡድን መዋቅር በመዘርጋት ህብረተሰቡን እያሰቃዩ የሚገኙትን ባደረግነው መራር የሚዲያ ትግል “የዋናዎቹ ቀንድ” የተሰበረ ቢሆንም እስካሁን ህብረተሰቡ እስከ ቀበሌ ድረስ እነሱ በፈጠሩት አደገኛ ህቡዕ አደረጃጀት ነፃ አልወጣም።

እንደሚታወቀው የዎላይታ ዞን በሀገሪቱ ከየትኛውም አከባቢ በላይ ወደ ሁለት መቶ ሺህ የሚጠጋ ከታወቁ ከፍተኛ ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች የተመረቁ የስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙበት ነው። በጨቅላ ዕድሜያቸው ከእናታቸው ተለይተው በሀገሪቱ ጎዳናዎች ሁሉ የስቃይ ህይወት እየገፉ የሚገኙት ህፃናት ፍልሰትም የችግሩ ስፋት የሚያመለክት ይሆናል። በአከባቢው በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት የወጣቶች የስራ ዕድል ከፍ የሚያደርጉ እንዱስትሪና ሌሎች ተቋማት አለመኖር ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ አባብሶታል።

በአከባቢው ያለውን ፀጋ በመጠቀም ሀገር ውስጥና ውጪ የሚገኙትን እንዲሁም ሁሉንም ህብረተሰቡን ለአንድ አላማ በማሳለፍ ችግሩ ከስሩ እንዲቀረፍ ለማድረግ የመምራት፣ የማስተባበርና የማስተዳደር ብቃት ያላቸው በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች እንዳይኖር ግለሰቦች በጥቅምና በዝምድና ተሳስረው ከፍተኛ ችሎታና ልምድ ያላቸው በየትኛውም ኃላፍነት ቦታ እንዳያገለግሉ በማግለል የዘረጉት አደረጃጀት ከፍተኛ ማነቆ እየሆነ ይገኛል።

ለመሆኑ እንደዚህ አይነት ህዝብን ለማገልገል ኃላፊነት ወስደው በጥቅምና በዝምድና ሰፊውን ማህበረሰብ በመግፋት የራሳቸው የሆነ ጥቂት አደረጃጀት በመዘርጋት ዘርፈብዙ ችግር እያስከተሉ የሚገኙትን ሌቦችን በማስወገድ በእውነተኛ ለውጥ የሚተጉትን እንዴት መተካት ይቻላል❓ ያንን ለማድረግ ከመንግሥት ምን ይጠበቃል ❓ ከህብረተሰብ ምን ይጠበቃል❓

የዎላይታ ህዝብ ከራሱ ሉአላዊ ሀገርነት ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለ ወዲህ አንድነቱ በተለያዩ ሴራዎች እንዲሸረሸር ከተደረገ በኃላ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአጋጣሚ በተገኙ የለውጥ ኃይሎች ከውስጥ የመነጨ ህዝባዊ ውግንና አስተባባርነት በአንድነት ለአንድ አላማ ያለ ምንም ልዩነት በሚያስደንቅ ሁኔታ የቆመውን ህዝብ የበተነው ማነው❓

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: