

ዶክተር ጉቼ ጉሌ ሱላ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመደቡ።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ከቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጋር የስራ ርክክብ ያደረጉ ሲሆን ከጥቅምት 16/2016 ዓ.ም ጀምሮ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሰሩ መመደባቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አሳውቋል።
ዶክተር ጉቼ ጉሌ ሱላ ከዚህ ቀደም በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በተመራማሪነት እና በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች በአመራርነት ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸው በመድረኩ ተመላክቷል።
ከቀናት በፊት የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮቹን በሙስናና በብልሹ አሰራር ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ወስኖ ለትምህርት ሚንስትር ማስተላለፉን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ መዘገቡ ይታወሳል።
አሁን በደረሰን መረጃ መሠረት ትምህርት ምንስቴር አድስ አመራሮችን በብቃታቸው አስፈትኖና አወዳድሮ ሳይሆን ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች በምደባ ኃላፊነት ቦታ እንደሰጣቸው ለማወቅ ችለናል።
በዚህም የቀድሞ ምክትል ፕረዝዳንት ዶ/ር ተክሌ ሌዛ ስቀር ሌሎች ሁሉም ከኃላፊነታቸው የተወገዱ ሲሆን በምትካቸው ዶክተር ጉቼ ጉሌ ሱላ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት በመሆን፣ ዶክተር ዘውድነህ ቶማስ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሰሩ፣ ዶክተር አክበር ጩፋ የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሰሩ መመደባቸው ተገልጿል።


የዩንቨርስቲው ቦርድ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ለትምህርት ሚኒስትር ያስተላለፈው ውሳኔ ባለፈው ወር ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ከዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የተውጣጣ የአመራሮችና የባለሙያዎች አጣሪ ኮሚቴ ከዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ሰፊ የግምገማና የውይይት መድረክ ላይ “አብዛኞቹ በአስተዳደራዊ እርምጃ የሚስተካከሉ ሳይሆን ከፍተኛ የህግ ጥሰት የተፈፀመበት በመሆኑ በየዘርፉ የተፈፀሙ ጥሰቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድበት” በሚል በተቀመጠው አቅጣጫ መነሻ ሀሳብና ሌሎች ተያያዥ ማስረጃ እንደሆነም መግለፃችን ይታወሳል። Wolaita Times