በዎላይታ መሬት በእንቨስትመንት ስም የወሰዱ ግለሰቦች ለአመታት ሳያለሙ ለህገወጥ ተግባር እያዋሉ መሆኑ ተገለፀ።

በዞኑ ለረጅም አመታት የተለያዩ “እንቨስትመንት ስራ ለመስራት” በሚል የወሰዱትን መሬት የተለያዩ ማጭበርበር መንገድ በመጠቀም ጉዳት እያደረሱ በመሆኑ አዳዲስ እንቨስትመንት ለመስራት የሚፈልጉ ወደ ዘርፉ ለመሰማራት እንቅፋት እየፈጠረ ስለመሆኑም ምንጫችን አስረድቷል።

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የግል ባለሀብት ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንዳስረዳው “በዞኑ ለረጅም ጊዜ የተለያዩ እንቨስትመንት ስራ ለመስራት በሚል ሰፊ መሬት ወስደው ሳያለሙ አጥሮ በማስቀመጥ ለአከባቢው እድገት ማነቆ ከመሆኑም ባሻገር መሬቱን ላልተፈለገ ህገወጥ አላማ” እያዋሉት እንደሆነ ተናግረዋል።

በዞኑ በገጠርና ከተማ በሆቴል፣ በግብርና፣ በማዕድንና በተለያዩ እንቨስትመንት ዘርፎች ሊለሙ የሚችሉ ሰፊ መሬቶች እንዲሁም ስራዎቹን ለማቀላጠፍ ከፍተኛ ስራ አጥ ወጣቶችና (የሰው ሀይል) ምቹ መልካ ምድር ያለበት ቢሆንም ጥቂት ግለሰቦች ውስን የሆነውን ህዝብና የመንግስት ሀብት የሆነውን ሰፊ መሬት በመያዝ በህገወጥ መንገድ አመራሮችን ተጠቅሞ የጥቅም ትስስር በመዝርጋት እየበዘበዙ እንደሆነ በመረጃ አጋልጠዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አንድ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የህግ መምህርና ጠበቃ ለረጅም አመት በእንቨስመንት ስም የወሰደ ግለሰብ መሬቱን ሳያለማ ወይንም ላልተፈለገ አላማ ካዋለ መፍትሔው ምንድነው ተብለው በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጠይቀው “በህጉ መሠረት የዞን እንቨስትመንት መምሪያና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እነዚህ ባለሃብቶች የተረከቡትን መሬት ( በከተማ ሆነ በገጠርም ) በመንጠቅ ለሌሎች አልሚዎች ማስረከብና እንደየሁኔታው የህግ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ቀጣይ በዘርፉ ለሚሰማሩት ትምህርት ይሆናል” በማለት አብራርተዋል።

የህግ ምሁሩ የዞኑ የዘርፉን ማነቆ ሲገልፁ “የተለያዩ ስራ ለመስራት በሚል ሰፊ መሬት የወሰዱት አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች ከመጀመሪያ ጀምሮ ከአመራሮቹ ጀምሮ እስከ ባለሙያዎች ድረስ በጥቅም ትስስር መሬቱን በእጃቸው ያስገቡ በመሆኑ የመንጠቅና በቀላሉ የህግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ጥበብና የህዝብ ውግንና ባለው ቁርጠኛ አመራር ካልተመራ ተፈፃሚነቱ አዳጋች” ነው ብሏል።

ከ10 ዓመት በላይ መሬቱን ሳያለሙ በእጃቸው ይዘው የቆዩ፣ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ለሌሎች የሚያስተላልፉ፣ የሚሸጡ፣ ካርታና ፕላን አስይዘው ከባንክ ብድር የሚወስዱ እንዲሁም ሌሎች እግዳያለሙ ቦታውን በመያዝ የአከባቢ ዕድገት ማነቆ የሚሆኑ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ትንሽ እንቅስቃሴ ሲጀመር ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታች ድረስ መዋቅር ድረስ የዘረጋቸው የጥቅም ተጋሪዎቻቸው በኩል ከባድ ጫና እየፈጠሩ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

ታጥረው በውስን ግለሰቦች እጅ እየተበዘበዘ የሚገኘው መሬት ለአልሚ ባለሀብቶች በማስተላለፍ ወይንም ባለሃብቶቹ እንዳያለሙ ያደረጋቸውን ችግሮችን በውይይት በመፍታት ወደ ልማት ቢያስገባቸው፤ ፈቃደኛ ካልሆኑ ደግሞ ለሌሎች አልሚዎች በህጋዊ መንገድ በማስተላለፍ በአከባቢው የሚገኙ ስራአጥ ወጣቶችንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የስራ ዕድል እንዲፈጠር እንዲሁም ዘርፉ ለአከባቢው ዕድገት በጎ ሚና እንዲጫወት ማድረግ ጊዜ የማይሰጥ የመፍትሔ ሀሳብ ነውና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *