አዲሱ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል “ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ ዝግጅት” በሚል ከመላው ህብረተሰብ መዋጮ መጠየቁ መነጋገሪያ ሆነ

አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ይፋዊ ምስረታ በሕዳር 13/2016 ዓ.ም በክልሉ ርዕሰ መዲና በሆነችው ዎላይታ ሶዶ ከተማ ከሁሉም ክልሎችና ፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የተጋበዙ እንግዶች በተገኙበት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከቀናት በፊት የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ታማኝ ምንጮችን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

ለክልሉ ይፋዊ ዝግጅት በሚል ለሚያካሂደው ዝግጅት እያንዳንዱ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ መንግስታዊ ተቋማት ፣ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋማት እንዲሁም ሁሉም ህብረተሰብ ክፍሎች መዋጮ እንዲያዋጡ ማለትም ዎላይታ 165 ሚሊዮን፣ ጋሞ 135 ሚ፣ ጌዴኦ 110ሚ፣ ጎፋ 80ሚ፣ ወዘተ መነሻ የገቢ ማሰባሰቢያ ዕቅድ መሸንሸኑን አንድ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ለWT ሚዲያ አስረድቷል።

“ይህን ያህል ገንዘብ እያንዳንዱ ዞንና ልዩ ወረዳዎች እንዲያዋጡ ከመደረጉ በፊት ህብረተሰቡን ግንዛቤ የማግኘትና የማሳመን ስራ መቅደም ነበረበት፤ በአመራሮች ደረጃ ተወያይተው በአስገዳጅነት ወደ ተግባር መግባት ትክክል አይመስለኝም ያለው የኮሚቴው አባል “ለክልሉ ምስረታ ገቢ አይሰበሰብ” የሚል አቋም ባይኖረንም ወቅቱን ባላገናዘበ መልኩ በሕዝብ ላይ ፍትሃዊ ያልሆነ የመዋጮ መጠን መወሰን ግን ተገቢ ስላይደለ መታረም አለበት” ብሏል።

አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የዎላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪና በዞኑ የገቢ አሰባሰብ ኮሚቴ አባል ለሚዲያችን ባደረሱት መረጃ “የመስከረም ወር 2016 ዓ.ም እንኳን ደመወዝ መክፈል ያልቻሉ 14 ወረዳዎችን አቅፎ የያዘው የዎላይታ ዞን አስተዳደርም የተደለደለለትን 165 ሚሊዮን ብር ከታችኛው መዋቅሮች፣ ከነጋዴዎች፣ ከተማሪዎች፣ ከአርሶ አደሮች፣ ከግል ድርጅቶች፣ ከሞተረኞች እንዲሁም ከሌሎች እንዲሰበሰብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል” ስል አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በዎላይታ ዞን ከ700,000 በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ሲሆን እእያንዳንዱ ተማሪ 200 ብር በነፍሰወከፍ በማዋጣት 140 ሚሊዮን ብር፤ አርሶ አደር 1,000 ብር፣ ነጋዴዎች 5,000 እስከ አንድ ሚሊዮን ብር፣ እያንዳንዱ ቀበሌ ከ200,000 በላይ እንዲያዋጡ የተጠየቀ ሲሆን ዎላይታ ሶዶ 72 ሚሊዮን፣ ቦዲቲ 16 ሚሊዮን፣ አረካ 15 ሚሊዮን፣ ወዘተ ገንዘብ እንዲሰበስቡ መመሪያ መሠጠቱንም የኮሚቴው አባል አስረድተዋል።

በሌላ በኩል አንድ የክንዶ ዲዳዬ ወረዳ ሞዴል አርሶአደር ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ ተጠይቆ “በቅርብ ጊዜ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ሦስት ዙር ከፍተኛ መዋጮ እንዲያዋጣ የተደረገው ሕዝብ በአሁን ወቅት ለክልል ምስረታ ተብሎ አባወራው ለብቻ፣ ልጆቹ በትምህር ቤት በኩል፣ ሚስቱ በዕድሩ በኩል፣ ወዘተ እየተባለ አንድ አባወራ እስከ አምስት ዓይነት መዋጮ ያለውን ሽጦ አልያም ተበድሮ ፍትሃዊ ያልሆነ መዋጮ እንዲከፍል ተብሎ ቀድሞ ሳይነገረን በድንገት መነገሩ አግባብ አይደለም” ስሉ ገልጸዋል።

“እያንዳንዱ አርሶ አደር የሚያደርገው መዋጮ ዓይነቶች፦ ማዐጤመ፣ የመሬት ግብር፣ ወልማ፣ የብልጽግና ፓርቲ መዋጮ፣ ለወረዳው ስፖርት ልማት፣ ቀይ መስቀል እና ድቻ ስፖርት ክለብ 1,200 ብር እንዲሁም ለደቡብ ክልል ምስረታ እስከ 1,000 በድምሩ ከ2,200 ብር በላይ በነፍሰወከፍ አርሶደአሮች እንዲከፍል ጫና እየተደረገ ሲሆን ከማይከፍሉት የእርሻ በሬንና የወተት በቀበሌ ሰንቴሪያ በማሰር ላይ ይገኛሉ፤ ከታሰሩ እንስሳትም በሚያሳዝን ሁኔታ የሞቱም አሉ” ስል ሞዴል አርሶአደሩ ለሚዲያችን ሁኔታውን አስረድተዋል።

ቀድሞ ሳይነገር ወደ ተግባር ተገብቶ ነጋዴዎች፣ ባንኮች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወዘተ ፍትሃዊ ያልሆነ መዋጮ እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው ከአመራሮች ጋር ከፍተኛ ጭቅጭቅና ውዝግብ እየተፈጠረ ሲሆን ወደ ግጭት እንዳያመራ እንዲሁም መዋጮው ያለ ሕጋዊ ደረሰኝ እጅ በእጅ እየተሰበሰበ በመሆኑ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል ለብክነትና ለሀብት ምዝበራ ምቹ ሁኔታም እንዳይፈጥርና በዚሁ አለመግባባት ምክንያት በአከባቢው ሌላ ችግር እንዳይፈጠር የሚመለከታቸው አካላት ጥብቅ ክትትልና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ የመስራት ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

ከልዩ ወረዳነት ወደ ዞንነት የተዋቀሩ አምስት የዞን መዋቅሮችን ጨምሮ አስር ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በአንድነት የመሰረቱት “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ክልል መንግስታዊ አገልግሎቶችን በተለያዩ ቦታዎች ጀምሯል ቢባልም ከተወሰኑት ውጪ አብዛኞቹ በሙሉ አቅማቸው አለመጀመራቸው በህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ እያስተናገደ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ህዳር 13/2016 ዓ.ም የአስተዳደርና የፓለቲካ ማዕከል በሆነችሁ ዎላይታ ሶዶ ከተማ ክልሉ በይፋ ስራውን ለመጀመር በሚያበስረው ዝግጅት ላይ “ለተለያዩ ልማት ስራዎች የሚውል ገቢ ከፌደራል፣ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ከተለያዩ ቦታዎች ከሚመጡ አመራሮችና ታዋቂ ግለሰቦች ለማግኘትና ክልሉ በሙሉ አቅም ስራውን ለመጀመር የሚያስችል ይፋዊ ዝግጅት ነው” በሚል የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ታማኝ ምንጭ ጠቅሶ መረጃውን ማድረሱ ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: