

ከ18 ዓመታት በላይ በሚዲያው ኢንዱስትሪ የቆየው ኦ ቢ ኤን ቴሌቪዥን ከወላይታ ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር የዎላይታቶ ቋንቋ ስርጭት ለመጀመር መዘጋጀቱን የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ገቢሳ ተናግረዋል፡፡
የቴሌቪዥኑ ስራ አመራር የዎላይታ ቴሌቪዥን ጣቢያን የጎበኘ ሲሆን ከስርጭቱ በተጨማሪ ተቋሙን በቴክኖሎጂ እና በአቅም ግንባታ ስራዎች ይደግፋል ብለዋል፡፡

ሚዲያዎቹ በጋራ ሲሰሩ የዎላይታን እና የኦሮሞን ህዝብ ለማቀራረብ ትልቅ ኃላፊነት ይወጣሉ የሚሉት የኦ ቢ ኤን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ተዘራ በቀለ የዎላይታ ቴሌቪዥንን በቴክኖሎጂ ዘርፍ በመደገፍ ውጤታማነቱን ለማሳደግ ታቅዷል ይላሉ፡፡
የዎላይታ ቴሌቪዥን በኦ ቢ ኤን ወላይታቶ ፕሮግራም ኦ ቢ ኤን ደግሞ በዎላይታ ቴሌቪዥን ኦሮሚፋ ፕሮግራም ለማሰራጨት የተጀመረው ንግግር የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነትን የሚያጠናክርና ሁለቱ ጣቢያዎች በጋራ መስራታቸው የውስጥ አቅማቸውን ከማጎልበት ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነትና ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክር እንደሆነ የዎላይታ ዞን የመንግስት ረዳት ተጠሪ ወ/ሮ መስከረም ደገፉ ተናግረዋል፡፡
የዎላይታ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሴባ ናና በበኩላቸው ኦ ቢ ኤን ብዙ ልምድ ያካበተ በመሆኑ በጋራ ለመስራት ሲወጠን የጣቢያውን ተጠቃሚነት በይዘትም በቴኬኖሎጂም ያጎላል ብለዋል፡፡

የኦ ቢ ኤን ቴሌቪዥን ስራ አመራሮች በዎላይታ ቴሌቪዥን ጽህፈት ቤት ካደረጉት ጉብኝት ባሻገር የጋራ ምክክር ያካሄዱ ሲሆን በአሰራሩ ላይ ከስምምነት ሲደረስ በቅርቡ የዎላይታቶ ቋንቋን በኦቢኤን ኦሮሚኛ ቋንቋን በዎላይታ ቴሌቪዥን ስርጭት ለማስጀመርም ታቅዷል ስል ዎቴቪ ዘግቧል። Wolaita Times