በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በሚካሄደው የሰላም ንግግር ላይ ለመሳተፍ በታንዛንያ የሚገኘው የጦሩ ዋና አዛዥ ኩምሳ ድሪባ “ፖለቲካ አያውቅም” የተባለው ሠራዊታቸው ኃያላን ባሉበት ለድርድር መቀመጡን ተናግረዋል።

መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን አዛዥ የሆነው ኩምሳ ድሪባ ይህንን የተናገረው ቅዳሜ ኅዳር 08/ 2016 ዓ.ም. በዙም አማካኝነት ከደጋፊዎቹ ጋር ባደረገው ወይይት ላይ ነው።

“ፖለቲካ አያውቁም፤ ልጆች ናቸው፤ አላማ የላቸውም። እርስ በርስ አይስማሙም ተብለን ስንናቅ የነበረው [የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት] ዛሬ ኃያላን ባሉበት እየተደራደርን እንገኛለን” በማለትም ተናግሯል።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይ ባለፉት ዓመታት ተባብሶ የዘለቀውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት እየተደረገ ያለው ሁለተኛ ዙር ንግግር ታንዛንያ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ ጃል መሮ ከአገር ሲወጣ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ከአስር ቀናት በላይ እየተካሄደ ያለው ይህ ውይይት መቼ እንደሚጠናቀቅም ሆነ በምን ዓይነት ጉዳዮች ላይ ንግግር እየተካሄደ እና ስለተደረሰበት ደረጃ እስካሁን ቢቢሲ በቂ መረጃ አላገኘም።

ለመጀመሪያ ጊዜ በታንዛንያዋ ከተማ ዳሬሰላም እየተካሄደ ባለው የሰላም ድርድሩ ላይ ተሳታፊ የሆነው ድሪባ ኩምሳ፣ በመካሄድ ላይ ስላለው የሰላም ድርድርን በተመለከተ ከደጋፊዎቹ ጋር በዙም አማካይነት ባደረገው አጭር ቆይታ ዝርዝር ነገር ከመናገር ተቆጥቦ “እየተናገርኩ ያለሁት ሻይ ሰዓት ላይ ነው” ሲል አስታውቋል።

“አሁን እየተካሄደ ስላለው ድርድር ይህ ነው፣ ያ ነው ማለት አልፈልግም። ነገር ግን ትልቅ ፈተና እንዳለብን ማወቅ አለባችሁ” ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

“በሥራችን ገምግሙን እንጂ በወሬ ብቻ አትመሥረቱ። እኛ ሥራ ላይ ነን” ሲልም ተደምጧል።

“የኦሮሞ ሕዝብ መወዳደር ያለበት በወሬ ሳይሆን በተግባር ነው። አንገታችሁን ደፍታችሁ በርትታችሁ ሥሩ። ታይታ ጥቅም የለውም” ብሏል።

የኦሮሞ ነጻነት እንቅስቃሴን እየደገፉ ላሉ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ባደረገው ንግግር “በገንዘብ ለምታደርጉት ድጋፍ እናመሰግናችኋለን። እኔ በበኩሌ ገንዘቡም ይቅር እያልኩ ነው። ሁሉም ሰው ባለው ሙያ እና ችሎታ እንዲደራጅ እፈልጋለሁ” ሲልም አስረድቷል።

“በሁሉም ነገር ባንስማማም እንዳልተስማማን አምነን በሰላም መኖር ራሱ እንደ አንድ ትግል ነው የማየው” ሲልም ተደምጧል።

አክሎም “እኛ መገንባት የምንፈልገው ሥርዓትን ነው። ለሚመጣው ትውልድ ምን ዓይነት ሥርዓት እና አገር እናስረክባለን የሚለው ነው የሚያሳስበን” አክሎም “እኛ እናልፋለን ነገር ግን ለመጪው ትውልድ ምን ዓይነት አሻራ ጥለን ነው የምናልፈው የሚለው ነው የሚያሳስበኝ” ብሏል የጦር አዛዡ።

የጦር አዛዡ ስለ ገንዘብ ጉዳይ ለምን እንዳነሳ ግልጽ ባይሆንም አንዳንድ መጭበርበሮች እንዳሉ ግን ጠቁሟል።

“ኦሮሞ ሌላ ፓርቲ መመሥረት” እንደሚችል የተናገረው ድሪባ ኩምሳ “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብቻ አይደለም። የራሳችሁ ፓርቲ መሥርቱ። ለዚህ ሰፊ ሕዝብ ብዙ ፓርቲዎች ቢኖሩት እኔ ተቃውሞ የለኝም። ነገር ግን በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስም ግን መነገድ ይቁም” ሲልም ለደጋፊዎቹ ተናግሯል ስል ቢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: