የ2013 ዓ.ም ከተማ ዐቀፍ የመሠረተ ልማት ንቅናቄ መድረክ በዎላይታ ሶዶ ተካሄደ!

በዎላይታ ሶዶ ከተማ በሚገነቡ አጠቃላይ መሠረተ ልማት ሥራዎች ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነትና ጥራትን ዙሪያ ከህዝቡ ጋራ የምክክር መድረክ ሰሞኑን ተደርጓል፡፡
በመድረኩ ከተለያዩ ህብረተሰቡ ክፍሎች የተወጣጡ ተወካዮች ከቀጠና ጀምሮ አስተባባሪዎች ፣ ከተለያዩ አደረጃጀቶች እንዲሁም በየአከባቢው የሚገኙ የመሠረተ ልማት ጥራት አምባሳደሮችና ሌሎችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
አቶ ዘካሪያስ ታደሰ የዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የምክክርና ውይይት መድረኩን በይፋ ባስጀመሩበት ንግግራቸው እንደገለፁት በከተማ በሚሠሩ በየትኛውም መሠረተ ልማቶች ህብረተሰቡ በሰፊው ሊሳተፍና ሊጠቀምም ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ ያለ ህብረተሰብ ተሳትፎ የትኛውንም ተግባር መፈፅም የማይታሰብ ነው ያሉት ከንቲባ ህብረተሰቡ መሠረተ ልማት ሥራዎችን ከመጀመሪያ ሳይት መረጣ እስከ ርክክብ ባሉ ሂደቶች በነቃ በመሳተፍ ችግሮችንም የጋራ በማድረግ ከመንግስት ጎን ሆኖ በቅንጅት ሊሠራ ይገባል በማለት አስተዳደሩም ህብረተሰቡ እንዲሳተፍ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና የመከታተል ጉዳዮችን በትኩረት እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡
አቶ ሽመልስ አጫ የዎላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳዳር ም/ከንቲባና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው ህዝቡ የመሠረተ ልማት ባለቤት ነው በማለት በየትኛውም መሠረተ ልማቶች ህብረተሰቡ በመሳተፍ መሰረተ ልማቶች የራሴ ናቸው በማለት ሊንከባከብም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ለህዝቡ አጠቃላይ የመሠረተ ልማት ማስፋፍያ ስትራቴጂ፣ የትግበራ ፖሊስዎች፣ የመሠረተ ልማት ጥራት ፣ ተደራሽነትና ፍትሐዊነት እንዲሁም የህብረተሰብ አጠቃላይ ተሳትፎና በመሳሰሉ ጉዳዮች የውይይት መነሻ ሀሳብ በሰነድ መልክ ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበት የጋራ ስምምነት እንደሚፈጠር ታውቋል ሲል የከተማው ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ዘግቧል፡፡