“አስታራቂ ተብለው የተመረጡ አካላት የችግሩ መሪ የነበሩትን አመቻች ማድረግ አይገባም” የአከባቢው ምሁራን

“ልዩነቶች በእርቅና በሰላማዊ ውይይት ተፈቶ ለህዝቡ ልማት ሁሉም በጋራ እንዲሰራ” በሚል በቅርቡ የተቋቋመው ኮሚቴ እንቅስቃሴ በዎላይታ ዞን አስተዳደር ተቀባይነት አላገኘም ተብሎ የተሰራጨው መረጃ በፍጹም የተሳሳተና በአከባቢው የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የተጀመሩ መልካም ጅምሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑን ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኮሚቴው ለዞኑ አስተዳደር በፃፈው ደብዳቤ ላይ ሁኔታውን ለማሳካት የሚያደርገው እንቅስቃሴ፦ “ይህ በጎ ዓላማ ለዎላይታ ህዝብ ጥቅም እስከሆነ ድረስ ዞኑ መድረኩን በማዘጋጀት ውይይት እንዲደረግ መቸገሩ ብዙ ጥያቄ የሚያጭር እና ግራ የሚያጋባ ሆኗል” ማለቱን ተከትሎ የዞኑ አስተዳደር ምላሽ ሲሰጥ ፦ “በራሳችን ተነሳሽነት መድረኩ እንዲመቻች አድርገን ኮሚቴ አስመርጠን ወደ ተግባር እንዲገባ ያደረግንበትን ጥረት ለማብጠልጠል የተደረገ አሳዛኝ ክስተት ነው” ብሎታል።

ይሁን እንጂ ዞኑ አሁንም በአከባቢው የተፈጠሩ አለመግባባቶች በሆደ ሰፊነትና በሀቀኝነት እንዲፈታ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ መድረክ እንዲመቻች ከመቸውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆኑን በመግለፅ ኮሚቴው ሌላ ልዩነት ለመፍጠር ከሚሞክር ችግሩን ለመቅረፍ እውነተኛ ሀሳብ በግልፅነት የሚያቀርብ ከሆነ ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጧል።

በተለይም አዲሱ የዞኑ አስተዳደር ሁሉም በጋራ ጉዳይ በሆኑ የህዝብ የልማት ፍላጎቶች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡና በአንድነት በመሰለፍ በጎ ሚና ሊወጡ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲደርስ ለሚደረግ ለየትኛውም ጥረት የዞኑ በር ሁልጊዜም ክፍት መሆኑን ከመጀመሪያው ጀምሮ ስገልጽ እንደነበርም አስታውሷል።

በሌላ በኩል በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳብ የሰጡት አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት “በዎላይታ የተከሰተው በተለይም በገዥው ፓርቲ  ሹማምንት መካከል የተፈጠረው መቃቃር በዕርቅና በተግባቦት ምዕራፉ እንዲዘጋ ብዙ የተማፀንን ቢሆንም አስታራቂ ተብለው የተመረጡ አካላት አካታችነት የጎደለው፣ የፀቡ  ጠንሳሽና የችግሩ መሪ የነበሩት የዕርቁ ተዋናይ እንጅ አመቻች ማድረግ እንደማይገባ” ተናግሯል።

አሁንም ቢሆን አንዱን ዕርቅ ፈላጊ ሌላውን ደግሞ ፀብ ፈላጊ አድርጎ መሳሉ አግላይነትና መቃቃሩን የሚያባብስ ለህዝቡ የማይጠቅም በመሆኑ ይህን በዕርቁ ሂደት ጅማሮ ላይ የተፈጠረውን አለመግባባት ለሰፊው ህዝብ ጥቅም በውስጥ መፍታት እንደሚገባም ምሁሩ አስረድተዋል።

“አለመግባባቱ እንዲፈጠርና የቀድሞ ወጣት አመራሮች እንዲታሰሩ፣ እንዲሰደዱ አልፎም የክልል ጥያቄአችን የፅንፈኞች ጥያቄ ነው ብለው ለጠቅላዩ በማቃጠር በአከባቢው ቀውስ እንዲፈጠር ያደረጉ አካላት አስታራቂ ሆነው መቅረባቸው ስህተት ነው። ዕርቅና ሁሉ አቀፍ ተግባቦት ያስፈልጋል። እውነተኛና የተሳካ መድረክ እንዲካሄድ ከተፈለቨገ ሂደቱ ግን በጣም ገለልተኛ በሆኑ አካላት ሊመራ ይገባል” በማለት ሀሳብ አጋርተዋል። Wolaita Times

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *