“ትግላችን በትንሽም ቢሆን በፖለቲካ አስተሳሰብ ወደቤቱ መመልከት የጀመረ የነቃ ትውልድ መፍጠር እየቻለ ነው” ስሉ የዎላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር ገለፁ

የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ጎበዜ ጎኣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም የተጀመሩ የፖለቲካ ትግልና እድገቱን በሚገባ ፍጥነት እንዳይሄድ ያደረገው ዋንኛው ምክንያትና ተግዳሮቶች ዙሪያ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አጭር ማብራሪያ አጋርተዋል።

አቶ ጎበዜ ሁኔታውን ሲገልፁ “ፖለቲካ ውስጥ ስንቀላቀል በምክንያትና በጥበብ የተመሠረተ፣ ከመነሻው የህዝብን ጥቅም ለማስከበር፣ በሁሉም ዘርፍ የበቃና የመደራደር አቅሙን የገነባ ዎላይታን ለመፍጠር የተጀመረ ትግል እንጂ እዛም እዚህም ሸቅጠን በህዝብ ስም ለመነገድ የተጀመረ ትግል አይደለም ወደፊትም አይሆንም” ብለዋል።

“የዎላይታን ህዝብ ከአፄዎቹ ዘመነ መንግስት ሥርዓት አንስቶ እስካሁኗ ቀን ድረስ ፖለቲካና ኤሌክትሪክን በሩቁ የሚል ማስፈራሪያን በማሰማት የሸዋ ፖለቲካ አጨብጫቢ እንዲሆንና ከሸዋ በኩል የሚመጣ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንጂ አዋጭ መንገድ በእጅህ ምንም የሚጠቅም ነገር የለም የሚለውን ደካማ የፖለቲካ ድስኩር ለማክሸፍም ጭምር በመሆኑ ትግላችን በትንሽም ቢሆን በፖለቲካ አስተሳሰብ ወደቤቱ መመልከት የጀመረ የነቃ ትውልድ ለመፍጠር ችለናል እየፈጠረንም እንገኛለን” ስሉ አስረድተዋል።

ሊቀመንበሩ “አሁን የጀመርነው የፖለቲካ ትግልና እድገቱን በሚገባ ፍጥነት እንዳይሄድ ያደረገው ዋንኛው ምክንያትና ተግዳሮት” በሚል በዘረዘሩት ነጥብ “ገዥዎቹ ህዝቡ በፖለቲካ እንዳይሳተፍ፣ ተዋናይ እንዳይሆንና የሚገባውን እንዳይጠይቅ በኢኮኖሚው እንድደቅቅ አድርጓል” ስሉ ስርዓቱን አጥብቀው ተችተዋል።

አቶ ጎበዜ የትግሉ ማነቆ በሚል አክለው ሲገልፁ “በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የአስተዳደር ተጠሪዎች ወይም መሪዎች በሞግዚትነት የሚቀመጡና ለህዝብ ጥቅም ደንታ የለላቸው፣ ከአፄዎቹ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በማዕከላዊ መንግስት ስልጣን የተቸራቸውና በህዝብ ስም ውክልና ያገኙ ግለሰቦች ለህዝቡ ከማገልገል ይልቅ ለክብራቸውና ለዝናቸው የሚቆረቆሩ በመሆናቸውና ህዝቡ አገልጋያቸው እንዲሆን በመስራታቸው ነው” ብለዋል።

በአጋጣሚዎች የሚፈጠሩ ጠንካራ መሪዎች ካሉም ለማዕከላዊ መንግስት እንደስጋት ስለሚታዩ ሳይቆዩ ከኃላፊነታቸው ማንሳትና ማጥፋታቸው እንዲሁም አንዳንድ የአማራጭ ፖለቲካ አስተሳሰብ እከተላለሁ የሚሉ የዎላይታ ተወላጆችም “የአንዲት ኃይማኖት የአንዲት ባንዲራና የልሙጧ ኢትዮጵያ አቀንቃኝና ንዋይ ወዳጅ” መሆናቸው የተጀመረው የፓለቲካ ትግል ወደፊት እንዳይጓዝ እንቅፋት እየሆነ መሆኑንም የዎላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አብራርተዋል።

አቶ ጎበዜ ከዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጋር የነባራቸውን አጭር ቆይታ ሲያጠቃልሉ “በአጠቃላይ ዘርፈ ብዙ መንገራገጮች የሞሉበት ትግል ቢሆንም የዎላይታ ቀጣይ ትውልድ ነፃነትና እኩልነት ሲባል የሚያስከፍለውን የትኛውንም መስዋዕት በመክፈል የህዝቡን መፃኢ እድል በማይነቃነቅ ዓለት ላይ ለመመስረት ሁሉም ዎላይታ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል የውዴታ ሳይሆን የህልውና መሆኑ መሰመር ይኖርታል” ስሉም ጥሪ አቅርበዋል። በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *