ለ15 ዓመት ገደማ ለዎላይታና አከባቢው የፍትህ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ፍርድቤት በመዘጋቱ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ ጉዳትና እንግልት መጋለጡ ተገልጿል።

አስተያየት ሰጪዎቹ “የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማዕከል ጎፋሳውላ መሆኑን መቃወም ሳይሆን ለበርካታ አመታት የነበረው የዎላይታ ሶዶ ምድብ ችሎት እንዲቀጥልና እንደየአስፈላጊነቱ ተጨማሪ ማስተባበሪያ ቢሮዎች በተለያዩ አማካይ ከተሞች ላይ በማደራጀት ህብረተሰብ ያለምንም እንግልት ፍትህ በቅርበት እንዲያገኝ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጥ ተግባር ቢሆንም ያ እስካሁን ባለመሆኑ ጉዳዩ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መገኘቱ “በጋራ እንደግ” መሪ አንግቦ የተነሳውን አዲሱ ክልል ስም የሚያጎድፍ አሳፋሪ ተግባር ነው” ስሉ ተግባሩን አውግዘዋል።

የቀድሞ ደቡብ/ብ/ብ/ህ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የዎላይታ ሶዶው ምድብ ችሎት ለዎላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ደራሼ፣ ኮንሶና ደቡብ ኦሞ አከባቢዎች በተቀማጭነትና ተዘዋዋሪነት የይግባኝ ሰሚ ችሎት አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በፓለቲካ ውሳኔ መዘጋቱ ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እየሆነ እንደሚገኝ ተገልጋዮች ቅሬታ አቅርቧል፡፡

ምድብ ችሎቱ የአዲሱን ክልል አደረጃጀት ተከትሎ በአጠቃላይ ለዎላይታና ወደ ሶዶ ለሚቀርባቸው አከባቢዎች ጭምር የፍትህ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ አሁን ላይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በተወሰነው ፓለቲካዊ አቅጣጫ መሠረት አገልግሎቱ ዋናው ቢሮ በሚገኝበት ብቻ እንዲሰጥ በመደረጉ ህብረተሰቡ ለገንዘብ፣ ለጊዜና ላልተፈለገ እንግልት መዳረጉን ከተለያዩ ቦታዎች በስፋት የሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አንድ በክልሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የህግ ባለሙያ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሁኔታውን ሲያስረዳ ፦ “ህብረተሰቡ በአቅራቢያቸው ፍትህ የማግኘት መብት አላቸው፤ የፍትህ ጉዳይ ለህዝቡ ከፖለቲካ ጉዳይ የበለጠ አንገብጋቢ ነው፤ የቀድሞ ክልል መዋቅር ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር ምድብ ችሎቶች ወደ ተገልጋይ ህዝብ ቀረብ ብለው ተደራሽ እንዲሆኑ ጥናት ተደርጎ ከ15 ዓመት በላይ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ጥናት መዝጋት ህግ ብቻ ሳይሆን እጅግ የሚያሳዝን መሰረታዊ የፍትህ መርህ የጣሰ ኢፍትሀዊ ተግባር ነው” ብለዋል።

“በአከባቢው አባዛኛዎቹ የዞን፣ የወረዳ ፍ/ቤቶች ከሰው ኃይል አደረጃጀት እስከ ዳኝነት ስነ-ምግባር ባላቸው ጉድለቶች የፍትህ አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥ ህዝብን እያማረረ ባለበት በዚሁ ወቅት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ህብረተሰቡ ላልተፈለገ እንግልት ተዳርገው ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዋቅር አግኝቶ ይግባኝ ይጠይቅ ማለት ድሓ ላይ ብቻ ሳይሆን ፍትህ ላይ ጭምር መሳለቅ ይሆናል” ስሉም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የህግ ባለሙያ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሁኔታውን አክለው አስረድተዋል። በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው።

በመሆኑም የዞን፣ የክልል፣ የፌደራል መንግስት እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ፍትህ የማጣት ችግር በአስቸኳይ እንዲፈታ እንዲያደርጉና ከህግና ከጥናት ውጪ አላግባብ የተዘጋው የዎላይታ ምድብ ችሎት እንዲከፈት እንደየአስፈላጊነቱ በሌሎች አከባቢዎችም ተጨማሪ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎቶች በአስቸኳይ ተከፍቶ በህብረተሰቡ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ እንዲሁም የዜጎች መሠረታዊ ፍትህ በቅርበት የማግኘት መብት እንዲረጋገጥ ጥሪ ቀርቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *