በጋሞ ዞን ከአስተዳደራዊ መዋቅር ጋር ለተያያዙ አለመግባባቶች አፋጣኝ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ አሳስበዋል፡፡

ኮሚሽኑ ዛሬ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ አስተዳደርና በዙሪያው ቀበሌ መካከል የተነሱ የአስተዳደር ጥያቄዎች አሁንም ለሰዎች ሞትና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት እየሆነ ይገኛል ብሏል፡፡

በአካባቢው በአስተዳደራዊ አከላለል በተነሳ አለመግባባት ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የጠቀሰው የኮሚሽኑ ሪፖርት ከእነኝህም መካከል ሦስቱ ምንም አይነት መሣሪያ ባልያዙበት ሁኔታ በፖሊስ ቁጥጥር ሥራ ከዋሉ በኋላ መሆኑ እንዳሳሰበው አስታውቋል።

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር በአቅራቢያው የሚገኘውን ቆላ ሻራ የተባለ የገጠር ቀበሌ ወደ ከተማ አስተዳደሩ ለማካለል አቅዶ መሥራት ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ያም ሆኖ የከተማው አስተዳደር ዕቅዱን ገቢራዊ ለማድረግ ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ቢያደርግም ከሥምምነት መድረስ እንዳልቻለ ነው የሚነገረው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቀበሌው በአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ሥር የሚካለል ከሆነ የእርሻ መሬታችን ሊወሰድብን ይችላል የሚል ሥጋት በነዋሪዎቹ ዘንድ በመኖሩ ነው፡፡ ይህ “ትካለላላችሁ”  “የለም አንካለልም” የሚለው የነዋሪዎቹ እና የከተማ አስተዳደሩ እሰጥ አገባ አሁን ላይ በአካባቢው ለተከሰተው ሞትና ሰብአዊ መብት ጥሰቶች መበራከት ምክንያት ሆኗል ነው የሚባለው።

በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና በዙሪያው ባለው የቆላ ሻራ ቀበሌ ጉዳይ “አሳስቦኛል” ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት በአካባቢው በዜጎች ላይ ደረሰ ያለውን ጉዳት የተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አውጥቷል፡፡

የክልሉ መንግሥት ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ መጠቆሙን ለዶቼ ቬለ የገለጹት የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ሃላፊ አቶ ኢማድ አብዱልፈታህ “በአካባቢው በአስተዳደራዊ አከላለል በተነሳ ግጭት ምንም አይነት መሣሪያ ባልያዙበት ሁኔታ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ መሬት ላይ በማስተኛት በጥይት ተደብድበው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ዩኒፎርም በለበሱ የጸጥታ አባላት መሞታቸው በምርመራው የተሰባሰበው መረጃ  ይጠቁማል” ብለዋል።

በቆላ ሻራ ቀበሌው ጥቃት የቤተሰብአባሎቻቸው ለተገደሉባቸው ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ በኮሚሽኑ ሪፖርት መጠቀሱን የገለጹት የኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ሃላፊ አቶ ኢማድ አብዱልፈታህ “በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ፤ እንዲሁም በቁጥጥር ሥር በዋሉ ሰዎች ላይ ድብደባ የፈጸሙ፣ በሰዎች ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ የተሳተፉ የክልሉ መንግሥት የጸጥታ አባላት ላይ አስፈላጊ የሆነ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ጠይቋል።

ዶቼ ቬለ ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት ዙሪያ የጋሞ ዞንንም ሆነ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራሮችን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት ያልተሳካ ሲሆን የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ በቆላ ሻራ ቀበሌ መሬትን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ የአካባቢው አመራሮች በቁጥጥር ሥራ እየዋሉ እንደሚገኝ በቅርቡ በተረጋገጠ የፌስ ቡክ ገጹ መግለጹ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *