በዎላይታ ሶዶ ከተማ ሰሞኑን “የመሬት ሊዝ ክራይ አልከፈሉም” የተባሉ ግለሰቦች በፓሊስ ታድነው እየታሰሩ መሆኑ ተገለፀ።

የከተማ አስተዳደሩ ድርጊት ህገወጥና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የህግ ባለሙያዎች ተናግሯል።

“ከአምስት አመት በፊት በሶዶ ከተማ 13ተኛ ዙር ሊዝ አሸንፈን መሬት ለመረከብ እስከዛሬ ስድስት አመት በመመላለስ ላይ የምንገኝ ዜጎች ነን። ሊዝ ተወዳድረን መሬት ሊያስረክቡን ያልቻሉት የዎላይታ ሶዶ ማዘጋጃ በየግዜው እየተመላለስን ጥያቂያችንን ሳይመልሱ ሊዝ ውዝፍ ካልከፈላችሁ ብለው ማስታወቂያ አወጡብን ብንጮህ ሰሚ አጣን” እባካችሁ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ለእኛ ድምፅ ሁኑልን ስሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተማፅነዋል፡፡

ሰሞኑን በከተማዋ የፓሊስ አባላት፣ የገቢዎችና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ባለሙያዎች ወደ ግለሰቦች ቤት ለቤት እየገቡ ውዝፍ “የመሬት ሊዝ ክፍያ አልከፈላችሁም” በሚል በርካቶችን ወደ እስር ቤት እየወሰዱ ስለመሆኑና በማስገደድና በማስፈራራት እያስከፈሉ እንደሆነ አንድ የአይን እማኝ በተጨማሪነት ተናግሯል።

በሌላ በኩል ከትናንት ወዲህ በዚህ ምክንያት ለእስር ከተዳረገ በኃላ በዛሬው ዕለት ከእስር የተፈታውና መሬትን በሊዝ ክራ በመግዛት ሰርተው እየኖረ የሚገኝ ግለሰብ እንዳስረዱት “ሁኔታው በጣም ያሳዝናል፣ ለአመታት በመንግስት አሰራርና ክትትል ባለማድረግ ክፍተት የቆየውን ክፍያ በድንገት በመምጣት ከህግ ውጪ እንደ ዱሪዬ ኃይልን በቀላቀለ አካሄድ ማሰርና ማስገደዳቸውን በከተማ አስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ አሳድሯል” በሚል አስረድተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አንድ ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ የህግ ባለሙያ ሲያስረዳ “የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ 721/2004 አንቀጽ 20/5/ ላይ “ወቅቱን ጠብቆ በማይፈጸም ዓመታዊ ክፍያ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘገዩ የብድር ክፍያዎች ላይ በሚጥለው የቅጣት ተመን መሰረት መቀጫ ይከፈላል” ይላል በሚል አስረድቷል።

የህግ ባለሙያው የመሬት ሊዝ ክራይ ውል ባለቤቶች “ገንዘብ ተቀጥቶ ክፍያውን ከመክፈል ውጭ የወንጀል ተጠያቂነት የለውም። በሌላ በኩል ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው ደንብ ቁጥር 123/ 2007 አንቀጽ 30/5 ላይ “በየዓመቱ በሚከፈለው ቀሪ የሊዝ ክፍያ ላይ የዓመቱ ወለድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማበደሪያ ተመን መሠረት ይከፍላል” ስል አብራርቷል፡፡

በተጨማሪም “አንድ ሰው የሊዝ መሬት ክፍያ በግዜ አልከፈለም ተብሎ ልታሰር ይችላል ? የሊዝ ክራይ አመት ካላለቀ በስተቀር ወለድ ይጨምራል አንጂ ድርጊቱ በወንጀል ያስከስሳል፤ ያሳስራል ወይ? በሚል የዎላይታ ተይምስ ሚዲያ ለጠየቀው የህግ ባለሙያው ምላሽ ሲሰጡ “አንቀጽ 31/2 ላይ ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 6 መሰረት የሊዝ ባለይዞታው የሊዝ ክፍያውን ለመክፈል በሚገባው የጊዜ ገደብ ውስጥ ካልከፈለ በየዓመቱ ክፍያውን ባለመክፈሉ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ በየደረጃው የሚሰጠው ሆኖ የሦስት ዓመት ውዝፍ ካለበት
ከአራተኛው ዓመት ጀምሮ ባለው ጊዜ አግባብ ያለው አካል ንብረቱን ይዞ በመሸጥ ለውዝፍ ዕዳው መክፈያ የማዋል ስልጣን አለው፡፡” ይላል እንጂ በወንጀል የሚያስጠይቅ ነገር የለም።” ብሏል።

ሌላኛው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የህግ ባለሙያ “የልዝ ውል ፍትህአብሔር ወንጀል ልሆን አይችልም። አንድ ተዋዋይ በውሉ መሠረት ግዴታውን እየተወጣ አይደለም ካለ መንግስት ውሉን በማፍረስ ንብረቱን እንደገና ለልዝ ጨረታ ያወጣና ግለሰቡ የከፈለው ቅድመ ክፍያ እና ያለማው ነገር በነፃና ገለልተኛ ባለሙያ ተተምኖ ከባንክ ወለድ ጋር ተመላሽ ተደርጎ ይዞታውንና ያለማውን ሃብት መንግስት በልዝ ውል በግልጽ ጨረታ ለ3ኛ ወገን ያስተላልፋል። ከዚህ ውጪ ማስር በራሱ ወንጀል ነው።” በሚል ሁኔታውን አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ድርጊት ህገወጥና ሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን በማስረዳት በሊዝ በተያዘ ቦታ ያለውን ንብረት ለመሸጥም በቅድሚያ በየዓመቱ ማስጠንቀቂያ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ሊሰጥ እንደሚገባም አስረድቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ የከተማ አስተዳደር አካላትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ቢሆንም ከህግ አንፃር ተጠይቆ በቂ ማብራሪያ የሰጡ የህግ ባለሙያዎች በተከታዮቻችን ስም እያመሰገንን ከተማዋ በድንገት በንግዱ ማህበረሰብ የተጀመረው ጅምላ መቅጣትና ማሰር ዘመቻ በፊት የከተማዋ ዕድገት ወሳኝ የሆነው ግብር በተገቢው እንዲሰበሰብ ከተፈለገ ለአመታት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተመሳጥረው በሙስና የበለፀጉ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ እርምት እርምጃ ተወስዶ በየቀኑ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት ዘላቂ አሰራር ተዘርግቶ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ቀድሞ መሰራት አለበት እንላለን። በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *