ከገጠመው አደገኛ በሽታ በበርካቶች ድጋፍ ታክሞ የዳነ ዶክተር ደመወዝ በመስሪያቤቱ ተከለከለ።

የቀድሞ የዎላይታ ሊቃ ተማሪ ዶ/ር ታዴዎስ ሻሜቦ በ “GBS” በተሰኘ በሽታ ታምሞ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል መግባቱን ተከትሎ “የዶክተሩን ህይወት እንታደግ” በሚል የታዘዘው መድኃኒት እንዲገዛ በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጨምሮ በርካቶች ባደረጉት ቀና ትብብርና ዘመቻ ከሀገር ውስጥና ከውጭ በተሰበሰበ ገንዘብ ድጋፍ ወደ ሙሉ ጤንነት መመለሱ ይታወሳል።

ሆኖም ግን ከአደገኛ በሽታ ብዙዎች ባደረጉት ድጋፍ የዳነው ዶክተር ታዲዮስ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ባደረሰው መሠረት “እኔ በዚህ በሽታ ላይ እያለሁ ደመወዜ ከሀምሌ 1/2015 ዓ/ም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ባላወኩት ምክንያት ታግዶብኛል” ስል ቅሬታ አቅርቧል።

ዶክተሩ ለጋሞ ዞን ገረሴ ከተማ አስተዳር ጨምሮ ለሌሎች ለሚመለከታቸው አካላት በፃፈው ደብዳቤ በህመም ምክንያት የታገደው ደመወዝ እንዲለቀቅ መጠየቁን አስረድቷል።

በደብዳቤውም “እኔ ዶ/ር ታዲዎስ ሻሜቦ በጋሞ ዞን የገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሰራተኛ ስሆን ድንገት በገጠመኝ ህመም በፀና ታምሜ ከአምና ግንቦት 2015 ዓ/ም ጀምሮ ለ5 ወር በአዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮንፈረንሲቭ ስፔሻላዝ ሆስፒታል በGBS በሽታ በጽኑ ታምሜ በታመምኩበት ወቅት እኔን ለማትረፍ ከሆስፒታሉ አስተዳደር ሰራተኛ እስከ ባለሞያ እንዲሁም አገር አቀፍ እና ከውጪ ሃገርም ጨምሮ ህይወቴን ለማትረፍ በብዙ ተራባብበዋል” ስል ገልጿል፡፡

“እኔ በዚህ በሽታ ላይ እያለሁ ደመወዜ ከሀምሌ 1/2015 ዓ/ም ጀምሮ ባላወኩት ምክንያት ታግዶብኛል፡፡ ስለታገደውም ደመወዝ ጉዳይ በቀን 05/03/2016 ዓ/ም ሆስፒታሉን በደብዳቤ ቢጠይቅም ምንም ምላሽ አላገኘውም” በማለት ዶክተሩ ቅሬታ አቅርቧል።

ዶክተር ታዲዮስ አክሎም “ከስራ እስካሁን መገለሌ ወድጄ እንዳልሆነ በማሰብ እና በአሁኑ ሰዓት ወደ ሥራ ተመልሼ መስራት የምችልበት አቋም ላይ ስለምገኝ እንዲሁም በማገገሚያ እረፍት ላይ ያለው ሰው ብዙ ነገር እንደሚያስፈልገው አስባችሁ ከሐምሌ 01/2015 ዓ/ም ጀምሮ ታግዶ የነበረው ደመወዜ እንዲለቀቅልኝ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ” ስል አብራርቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ የሚመለከታቸው የተባሉ አመራሮችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም አሁን ላይ ከከባድ በሽታ በበርካቶች ዕገዛ ድኖ ከስራና ከደሞዝ ታግዶ ችግር ላይ የሚገኘው ዶክተር ታዲዮስ ፍትህ እንዲያገኝ መረጃውን ለበርካቶች በማድረስ እንድትተባበሩ ጥሪ እናቀርባለን። በናትናኤል ጌቾ የተፃፈ ዜና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *